Saturday, September 25, 2021

የመስቀል በዓል ታሪካዊ አመጣጥ

የመስቀል በአል ታሪካዊ አመጣጥ 


የመስቀል በዓል ስናከብር ልናጤነው የሚገባን ዐቢይ ቁም ነገር አይሁድ ክርስቶስ የተሰቀለበትን መስቀል ቆሻሻ ማጠራቀሚያ ቦታ በመቅበር እንዲረሳ ለማድረግ ቢሞክሩም በንግሥት ዕሌኒ አማካኝነት እንዴት እንደተገኘና የቀኝ እጁ የተቸነከረበት ክፋይ ወይም ግማድ እንዴት ወደ ሀገራችን እንደመጣ እንቃኛለን፡፡ መልካም የመስቀል በዓል ይሁንላችሁ!

የመስቀል በዓል ታሪካዊ አመጣጥ

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሰው ልጆችን ለማዳን የተሰቀለበት ቅዱስ መስቀል ሕሙማንን በመፈወሱ ምክንያት በርካታ አሕዛብ ክርስቲያን እንዲሆኑ አስችሏል፡፡ በተአምራዊነቱና በክርስቲያኖች ዘንድ ከፍተኛ ክብር የተሰጠው በመሆኑና ይህን የተመለከቱ አይሁድ ቅዱስ መስቀሉን በአንድ የቆሻሻ ማጠራቀሚያ ቦታ እንዲቀበር አደረጉ፡፡ የአካባቢው ነዋሪዎች በየቀኑ ቆሻሻ ስለሚጥሉበት ቦታው ወደ ተራራነት ተቀየረ፡፡ ምንም እንኳን መስቀሉን ለማውጣት ባይችሉም በኢየሩሳሌም የነበሩ ክርስቲያኖች ቦታውን ያውቁት ነበር፡፡ በሰባ ዓመተ ምሕረት በጥጦስ ወረራ ኢየሩሳሌም ስለጠፋች በዚያ የነበሩ ክርስቲያኖች ተሰደዱ፡፡ የተቀበረበትን ቦታ የሚያውቅ ባለመገኘቱ መስቀሉ ከ300 ዓመታት በላይ ተዳፍኖ /ተቀብሮ/ ኖረ፡፡

በ326 ዓ.ም. የንጉሥ ቆስጠንጢኖስ እናት ንግሥት ዕሌኒ ቅዱስ መስቀሉን ለመፈለግ ወደ ኢየሩሳሌም ጉዞ አደረገች፡፡ እዚያም ደርሳ ጉብታ የሆነውን ሁሉ ብታስቆፍር መስቀሉ ያለበትን ቦታ ማግኘት አልቻለችም፤ ሰውም ብትጠይቅ የሚያውቅ አልተገኘም፡፡ በመጨረሻም የመስቀሉ መገኘት የእግዚአብሔር ፈቀድ ነበርና አንድ ይሁድ አረጋዊ የታሪክ አዋቂና ሽማግሌ አግኝታ ቅዱስ መስቀሉ የተቀበረበትንና የተጣለበትን አካባቢ ያውቅ ዘንድ ጠየቀችው፡፡ ሽማግሌውም “አንቺም በከንቱ አትድከሚ ሰውንም አታድክሚ እንጨት አሰብስበሽ እጣን አፍሽበት በእሳትም አያይዢው የእጣኑ ጢስ ወደላይ ወጥቶ ወደታች ሲመለስ አቅጣጫውን አይተሽ አስቆፍሪው በዚህ ምልክት ታገኚዋለሽ” አላት እርሷም ያላትን ሁሉ አደረገች። እንጨት ደምራ በዚያ ላይም ዕጣን ጨምራ በእሳት ለኮሰችው፤ የዕጣኑ ጢስ ወደ ላይ ወጥቶ ወደ ታች ሲመለስ መስቀሉ ያለበትን ቦታ በጣት ጠቅሶ እንደማሳየት ያህል አመለከተ፡፡ ንግሥት ዕሌኒም ጢሱ ያረፈበት ቦታ ቅዱስ መስቀሉ የተቀበረበት እንደሆነ አመነች፡፡ ይህ ይሁድ አረጋዊ የታሪክ አዋቂና ሽማግሌ በኋላ በክርስቶስ አምኖ ተጠምቋል፤ ስሙም ኪርያኮስ ተብሏል፡፡

በዚህም መሠረት ከመስከረም 17 ቀን አስጀምራ እስከ መጋቢት 10 ቀን ሌሊትና ቀን ለሰባት ወራት ያህል የጉድፍን ኮረብታ ቆፍረው ቆሻሻውንም ካስወገዱ በኋላ ሦስት መስቀሎች ተገኙ ፡፡ የጌታም መስቀል ሙት በማስነሣቱ ተለይቶ ታውቋል፡፡ መስቀሉ የተገኘው መጋቢት 10 ቀን 326 ዓ.ም. ነበር፡፡ ቅድስት ዕሌኒ ይህን ተአምር በማየቷ እጅግ ደስ አላት፡፡ ሕዝቡም ሁሉ መስቀሉን እየዳሰሱ ኪርያላይሶን እያሉም በመዘመር ደስታና ሐሴት አደረጉ፡፡ ቀኑ መሽቶ ጨለማ በሆነ ጊዜም የኢየሩሳሌም ጳጳስ ብፁዕ አቡነ መቃርዮስና ንግሥት ዕሌኒ፣ ሠራዊቱና ሕዝቡ በሰልፍ በችቦ መብራት መዝሙር እየዘመሩ ቅዱስ መስቀሉን ወደ ቤተ ክርስቲያን ወስደው በአንድ የጸሎት ቤት አኖሩት፡፡ በኋላም በንጉሥ ቆስጠንጢኖስ ዕብነ መሠረት ወይም የመሠረት ድንጋይ ተቀምጦ ለመሰቀሉ መታሰቢያ ቤተክርስቲያን ተሠርቶ ተመርቆ የገባው (ቅዳሴ ቤቱ) የተከበረው መስከረም 17 ቀን 327 ዓ.ም. ነው፡፡ በቤተ ክርስቲያናችን ሁለቱም ዕለታት ይከበራሉ፤ በደማቅ ሁኔታና በመጀመሪያ ደረጃ የሚከበረው ግን መስከረም 17 ነው፡፡ ይህም የሆነበት ምክንያት መጋቢት 10 ቀን ሁልጊዜም በዐቢይ ጾም ወቅት የሚውል መሆኑና ለመስቀሉ የተሠራው ቤተ መቅደስ የተከበረው መስከረም 17 በመሆኑ ነው፡፡

ይህ ዕለት ከ300 ዓመታት በላይ ጠፍቶ የነበረውን ቅዱስ መስቀል በንግሥት ዕሌኒ አማካኝነት መገኘቱን የምንዘክርበት በዚህም ደስ የምንሰኝበት ዕለት ነው፡፡ ይህን መነሻ በማድረግ በኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ደመራ በመደመር የመስቀል በዓል በታላቅ መንፈሳዊ ሥነ ሥርዐት ይከበራል፡፡


የደመራ ትርጉም

ደመራ የሚለው ቃል – ደመረ፣ ጨመረ፣ አንድ አደረገ፤ ከሚለው የግእዝ ቃል የተወረሰ ሲሆን መቀላቀልን፣ መገናኘትን፣ መሰብሰብን፣ መጣመርን፣ መዋሐድን በአጠቃላይ ሱታፌን፣ አንድነትን እና ኅብረትን ያመለክታል፡፡ ቅዱስ መስቀሉ በተገኘበት ቦታም ስለሆነም ደመራ እንጨቶች የሚደመሩበት የበዓለ መስቀል ዋዜማ ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያናችን ከምታከብራቸው ዘጠኙ የጌታችን ንዑሳን በዓላት አንዱ በዓል ነው፡፡ መስቀል የሰላማችንና የድኅነታችን የመቀደሳችን ዓርማ፣ ኢየሱስ ክርስቶስ የሰውን ልጆች ለማዳን፥ የዘላለም ሕይወትን ለመስጠት መስዋዕትነት የከፈለበት ቅዱስ ሥጋውን ክቡር ደሙን ያፈሰሰበት መንበር፥ ሲሆን አምላካችንን የምንመለከትበት መስታወት ነው።


በሀገራችን በኢትዮጵያ የመስቀልን በዓል ደመራ በመደመርና ችቦ በማብራት፥ ቅዳሴ በመቀደስና ማኅሌት በመቆም የምናከብረው ለዚህ ነው። በዚሁም ላይ ይህን ታላቅ ዕፀ መስቀል በወቅቱ የነበሩ ታላላቅ ነገሥታት የሚያደርጋቸውን ተዓምራት በማየት ለእያንዳንዳቸው ይደርሳቸው ዘንድ ከአራት ክፍል ሲከፍሉት ከአራቱ አንዱ የቀኝ እጁ ያረፈበት ግማድ /ክፋይ/ ብቻ በደብረ ከርቤ ግሸን ማርያም ሲገኝ ሌሎች ሦስቱ ግን የት እንደደረሱ አይታወቅም።


መስቀሉ እንዴት ወደ ሀገራችን መጣ?

የጌታችን ቅዱስ መስቀል ወደ ሀገራችን ሊመጣ የቻለበት 1394 ዓ.ም. ሁለተኛ በነገሡ በ29ኛ ዓመታቸው የእስክንድርያ ቤተ ክርስቲያን ሊቀጳጳስ ብፁዕ አቡነ ሚካኤል 47ኛ በወቅቱ የነበረው የግብጽ ፈርዖን አሠራቸው ክርስቲያን የሆኑ ዜጎቹን “የእኔን ሃይማኖት ካልተከተላችሁ በግብጽ መኖር አትችሉም” ብሎ ከአቅማቸው በላይ ግብር ጣለባቸው፡፡ መከራው የጸናባቸው የግብጽ ክርስቲያኖች “ከደረሰብን መከራና ሊቀጳጳሳችንን ታስፈታልን ዘንድ በእግዚአብሔር ስም ተማጽነናል” ሲሉ ለአፄ ዳዊት መልእክት ላኩባቸው፡፡
አፄ ዳዊት “ክተት ሠራዊት ምታ ነጋሪት” ብለው አዋጅ በማወጅ ጦርነት ለማካሔድ ወስነው ወደ ካርቱም ጦራቸውን አዘመቱ፡፡ ካርቱም ደርሰው ሁኔታውን ሲያዩ ጦርነት ከማካሔድ ለምን የዐባይን ወንዝ አልገድብም ብለው ወሰኑ፡፡ ይህንንም ተግባራዊ ለማድረግ እንቅስቃሴ ማድረግ ጀመሩ፡፡ ይህን የሰሙ የወቅቱ የግብጽ መሪ መርዋን እልጋዴን መኳንቱን ሰብስበው “ምን ይሻለናል ብለው ምክር ያዙ” የዐባይን ወንዝ ከምናጣ “ሊቀጳጳሱን አቡነ ሚካኤልን እንፈታለን በክርስቲያኖችም ላይ መከራ አናደርስም” ብለው ቃል በመግባት ብፁዕ አቡነ ሚካኤልን ሁለት እልፍ ወቂት ወርቅ እጅ መንሻ አስይዘው ለዐፄ ዳዊት አማላጅ ላኩ፡፡
ንጉሡ ዐፄ ዳዊትም “ብርና ወርቅ አልፈልግም ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ የተሰቀለበትን መስቀል ነው የምፈልገው” አሏቸው፡፡ የሀገራችን ሕዝብ በውኃ ጥም ከሚያልቅ ብንስማማ ይሻለናል ብለው መስከረም 10 ቀን 1395 ዓ.ም. ከመስቀሉ ጋር ቅዱስ ሉቃስ የሳላት የእመቤታችን ሥዕል ጨምረው ሰጧቸው፡፡ በየዓመቱ መስከረም 10 ቀን የተቀጸል ጽጌ /የዐፄ መስቀል/ እየተባለ የሚከበረው ይህን መነሻ በማድረግ ነው፡፡
የታላቋን ንግሥት ዕሌኒን ታሪክ በማስታወስ መስከረም 17 የመስቀል በዓልን ካከበሩ በኋላ “መስቀልየ ይነብር በዲበ መስቀል /መስቀሌ በመስቀል ላይ ይኖራል/” የሚል ራእይ ታያቸው፡፡ “ይሔ ነገር ምሥጢሩ ምንድን ነው?” እያሉ በድንገት ሲናር ላይ አርፈው አጽማቸው ዳጋ እስጢፋኖስ አርፏል፡፡


በእሳቸው እግር የተተኩት ልጃቸው ዐፄ ዘርዓ ያዕቆብ “አንብር መስቀልየ በዲበ መስቀል /መስቀሌን በመስቀልያ ስፍራ አስቀምጥ/” የሚል ራእይ በተደጋጋሚ እግዚአብሔር አሳያቸው፡፡ በኢትዮጵያ ካሉት መልከዐ ምድር ውስጥ የመስቀል ቅርጽ ያለው የቀራንዮ አምሳል የሆነ ቦታ ከፈለጉና ካጠኑ በኋላ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶሰ በቀራንዮ የተሰቀለበት ቀኝ እጁ ያረፈበት ግማደ መስቀል አሁን ግሼ አምባ በሚባለው ሥፍራ ላይ መስከረም 21 ቀን 1446 ዓ.ም ደብረ ከርቤ አሁን እግዚአብሔር አብ ቤተ ክርስቲያን የታነጸበት ቦታ ላይ እንዲያርፍ አደረጉ፡፡



ግሸን ደብረ ከርቤ ማርያም ገዳም 

የግሸን ደብረ ከርቤ ማርያም ገዳም ወሎ ክፍለ ሃገር፣ አምባሰል ወረዳ ውስጥ ግሸን ተራራ አናት ላይ የምትገኝ ቤተ ክርስቲያን ናት። ለዚች ቤተ ክርስቲያን መግቢያ አንድ መንገድ ብቻ ነው። እንደ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ትውፊት ይህች ቤተ ክርስቲያን በየዘመኑ የተለያየ ስያሜን አግኝታለች።

የግሸን ደብረ ከርቤ ማርያም ገዳም መጠሪያ ስሞች

ግሸን ደብረ ከርቤ ማርያም ገዳም መጠሪያ ስሞች በተለያዩ ዘመናት የተለያዩ እንደነበር የታሪክ ድርሳናት ይነግሩናል፡፡
 ከዐፄ ድልናኦድ ዘመን /866 ዓ.ም/ እስከ 11ኛው ክፍለ ዘመን በአሁኑ ስያሜ /ደብረ ከርቤ/ ትታወቅ ነበር።
• በ11ኛው ክፍለ ዘመን አጼ ላሊበላ ከቋጥኝ ድንጋይ ፈልፍለው እግዚአብሔር አብ የተሰኘ ቤተ ክርስቲያን በዚሁ ቦታ ሲያሰሩ ደብረ እግዚአብሔር በሚል ስም ታወቀች። ብዙ ሳይቆይ ግን ደብረ ነገሥት ተባለች።
• በ1446 ዐፄ ዘርዓ ያዕቆብ ግማደ መስቀሉ በዚህ ስፍራ ሲያርፍ ደብረ ነገሥት መባሏ ቀርቶ ደብረ ከርቤ ተባለች።
ዐፄ ዘርዓ ያዕቆብ ግማደ መስቀሉን ይዘው እየገሰገስገሱ ስለመጡ በግዕዙ “ገሰ” ወይም በአማርኛው “ገሰገሰ” የሚለው ቃል ለቦታው ስያሜ ሆነ። በዘመናት ሂደት ገስ ወደ ግሸን የሚለው ስያሜ ተቀየረ። አካባቢው በዚህ ስም እንደተጠራ የግሸን ደብረ ከርቤ ገዳም ታሪክ የጻፉት የመሪጌታ የማነ ብርሃን አዲሴ መጽሐፍ በስፋት ይነግረናል፡፡ የግሸን ደብረ ከርቤ ገዳም ታሪክ በስፋት ለማወቅ የምትፈልጉ ወገኖቻችን መጽሐፋቸውን ብታነቡ ተጨማሪ መረጃ ማግኘት ትችላላችሁ እያልን በዚሁ እንሰናበት፡፡ 

በቸር ያገናኘን!

Sharing is caring

Tuesday, September 7, 2021

ሎጊታና ገላና የሲዳማ ጸጋዎች፤ የኢትዮጵያ አዲስ ሀብቶች

 ሎጊታና ገላና የሲዳማ ጸጋዎች፤ የኢትዮጵያ አዲስ ሀብቶች 


(ተጓዡ ጋዜጠኛ ሄኖክ ስዩም ሲዳማ ክልል ስደርስ ድባቡ ሁሉ የእናት ሀገር ጉዳይ ነው፡፡ የሲዳማ ልቡ ሰሜን ኢትዮጵያ ዘልቋል፡፡ መንደሮቹ ለሀገር መከላከያ ሠራዊት ደጀን ለመሆን ያላቸውን ይለግሳሉ፤ ከተሞቹ ወኔ ቀስቃሽ ናቸው ሲል እስከ ሎጊታና ገላና ፏፏቴዎች ያደረገውን ጉዞ እንዲህ ያጋራናል፡፡)



(ሄኖክ ስዩም -ድሬ ቲዩብ)

ሲዳማ ነኝ፡፡ የገባሁበት ሁሉ በሀገር ጉዳይ መንፈስ ታውዷል፡፡ የሲዳማ ልቡ ሰሜን ላይ ነው፡፡ የእናት ሀገሩን ውሎ ያደምጣል፡፡ ብዙ ቦታዎች ስለ ሀገር ፍቅር፣ ስለጁንታው መደምሰስ የሚገልጹ ጽሑፎችን አይቻለሁ፡፡

ከሀዋሳ ደቡብ ምስራቅ አቅጣጫ 119 ኪሎ ሜትር ተጉዤ የደርስኩበት ይህ ስፍራ የሲዳማ ሌላ ውበት በድንቅ የፏፏቴ ዜማ የሚደመጥበት ቀዬ ነው፡፡ አዲሱ ክልል በነባሩ የሀገራችን የቱሪዝም ልማት ላይ ብዙ ድብቅ ገጸ በረከቶችን ይዞ የመጣ ነው፡፡ አንዱ ጋር ደርሻለሁ፡፡

ቦና ወረዳ ይባላል፡፡ እዚህ አስደናቂዎቹ መስህቦች ይታያሉ፡፡ አሁን እኔ ሎጊታ ስር ቆሜያለሁ፡፡ ሎጊታ ከአርቤጎና ምድር ከጋራምባ ተራራ የሚመጣ ወንዝ ነው፡፡ እንዲህ ያለ ቦታ ሆኖ የሚታየውን ተአምርና አስደናቂ ሁኔታ የትም የለም፡፡

አካባቢው ውብ ነው፡፡ የሎጊታ ወንዝ ድንቅ መልከዓ ምድር ፈጥሯል፡፡ አካባቢው ውብና ለመንገድ ቅርብ ነው፡፡ ያቆሙትን መኪና በርቀት እያዩ የሚጎበኙት ፏፏቴ መሆኑ ከሀገሬ ፏፏቴ ልዩ ያደርገዋል፡፡

የሎጊታን ወንዝ ጉዞ ተከትዬ ሌላ ስፍራ ደረስኩ፡፡ ጋላና ወንዝ ደግሞ ሌላ ፏፏቴ ሰርቷል፡፡ አንድ ጊቢ ሁለት የታላላቅ ወንዝ ፏፏቴዎች አንዱ ጋር ሲደርሱ የሌላው ድምጽ እየሸኘ ውበት የሚታይበት፡፡

እነኚህ ሁለት ወንዞች ከፏፏቴዎቻቸው ግርጌ አንድ ሆነው ይዋህዳሉ፡፡ የሚዋህዱበት አፋፍ ቆሜ አየሁ፡፡ ጋላና እና ሎጊታ ስማቸው ከዚህ በኋላ አንድ ነው፡፡ ገናሌን ፈጥረዋል፡፡ ገናሌ ከጋራምባ መሀጸን ብዙ ምንጭ ሆኖ በተበተነ ውበት ሁለት ወንዝና ፏፏቴ ሆኖ በአንድ ስም ለመጠራት አንድ ወንዝ የሚሆንበት ስፍራ፤

ገናሌ ተጓዥ ወንዝ ነው፡፡ መንገደኛነቱን ከሚያሳዩን መረጃዎች አንዱ 858 ኪሎ ሜትሮችን የሚፈስ መሆኑ ነው፡፡ ከዚያ ውስጥ በእናት ሀገር ምድሩ 480 ኪሎ ሜትሮችን ይጓዛል፡፡ እነሆ እዚህ አንድ ብሎ እና ገናሌ ተብሎ ከሎጊታና ከገላና ወንዞች ተዳቅሎ ሲፈጠር እያየሁ ነው፡፡

የቀድሞዎቹ የባሌና ሲዳሞ ጠቅላይ ግዛቶች ድንበር የዛሬው የገናሌ ዳዋ ሃይል ማመንጫ ሀብት የሚፈጠርበት ቆሞ እንዲህ ማሰብ ደስ ያሰኛል፡፡

ወልመልና ወይብን ተቀላቅሎ ወደ ጁባ የሚገባው ወንዝ ምንኛ ደጋ ምድር ፈጠረው ብዬ ሌላ ስፍራ ለማየት ጓጓሁ፡፡ እናም ወደ ሲዳማ ደጋ ምድር ለመውጣትና የአርቤጎናን ምንጮች ለመመልከት ልጓዝ ነው፡፡

ግቢውን ለቅቄ ስወጣ ይከተለኝ የነበረው የጋላና ፏፏቴ ድምጽ ለሎጊታ ፏፏቴ አቀብሎኝ እስከ አስፋልቱ ጎዳና ሸኘኝ፡፡

አሁን አብረን ደጋማው የሲዳማ ምድር እንጓዛለን፡፡ በረደኝ የለም በሻፌታ ይቀርባል፡፡ የእርጎ ሀገር ነው፡፡ ንጹህ ቅቤ የሚገኝበት፡፡ የሲዳማ ጎጆ ለእንግዳ ቸር ነው፡፡ ያንን ለማየት እነዚህ መንደሮች መግባት ይጠይቃል፡፡


https://news.et/2021/09/03/%e1%88%8e%e1%8c%8a%e1%89%b3%e1%8a%93-%e1%8c%88%e1%88%8b%e1%8a%93-%e1%8b%a8%e1%88%b2%e1%8b%b3%e1%88%9b-%e1%8c%b8%e1%8c%8b%e1%8b%8e%e1%89%bd%e1%8d%a4-%e1%8b%a8%e1%8a%a2%e1%89%b5%e1%8b%ae%e1%8c%b5/