Saturday, December 28, 2019

እንኳን ለቅዱስ ገብርኤል በዓል በሰላም አደረሳችሁ

በስመአብ ወወልድ ወመንፈስቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን
እንኳን ለቅዱስ ገብርኤል በዓል በሰላም አደረሳችሁ

የቅዱስ ቂርቆስ እና ቅድስት ኢየሉጣ ተጋድሎ

በመጽሐፈ ስንክሳር፣ በድርሳነ ገብርኤል እና በገድለ ቂርቆስ ወኢየሉጣ እንደ ተመዘገበው ሐምሌ ፲፱ ቀን ቅዱስ ቂርቆስ እና ቅድስት ኢየሉጣ በሰማዕትነት መከራ የተቀበሉበት፤ ስማቸውን የሚጠሩ፣ ዝክራቸውንም የሚዘክሩ ምእመናን ይቅርታን፣ ምሕረትን እንደሚያገኙ ጌታችን አምላካችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለእነዚህ ቅዱሳን ቃል ኪዳን የሰጠበት ቀን ነው፡፡ መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ከእግዚአብሔር ዘንድ ተልኮ የተራዳቸውም በዚሁ ዕለት ነው፡፡ በዛሬው ዝግጅታችን የሰማዕታቱ ቅዱስ ቂርቆስንና ቅድስት ኢየሉጣን ገድል በአጭሩ እናስታውሳችኋለን፤
ቅድስት ኢየሉጣ በሮም ግዛት በሚገኝ አንጌቤን በሚባል አገር በፈሪሃ እግዚአብሔር፣ በክርስትና ሃይማኖት እና በበጎ ምግባር ጸንታ ትኖር የነበረች ደግ ሴት ናት፡፡ በሥርዓት ያሳደገችው ቂርቆስ የሚባል ሕፃን ልጅም ነበራት፡፡ ይህቺ ቅድስት የዘመኑን አረማዊ መኰንን እለእስክንድሮስን በመፍራቷ ከልጇ ጋር ከሮም ወደ ጠርሴስ በተሰደደች ጊዜ መኰንኑ እነርሱ ከሚገኙበት አገር ገብቶ ክርስቲያኖችን እያሳደደ መግደል ጀመረ፡፡ የንጉሡ ወታደሮችም እግዚአብሔርን እንዲክዱ፤ ለጣዖት እንዲሰግዱ ቅድስት ኢየሉጣንና ቅዱስ ቂርቆስን አስፈራሯቸው፡፡ ቅዱሳኑ ግን ሃይማኖታቸውን ለመለወጥ ፈቃደኛ አልኾኑም ነበር፡፡ በዚህም መኰንኑ ተቈጥቶ በዓይንና በአፍንጫቸው ውስጥ ጨውና ሰናፍጭ በመጨመር፤ በጋሉ የብረት ችንካሮች በመቸንከርና መላ ሰውነታቸውን በመብሳት በብዙ ዓይነት መሣሪያ አሠቃያቸው፡፡ እግዚአብሔርም የጋሉ ብረቶችን እንደ ውኀ ያቀዘቅዝላቸው፤ ሥቃያቸውንም ያቀልላቸው ነበር፡፡
በሌላ ጊዜም በገመድ አሳሥሮ ንጉሡ ሲያስጨንቃቸው ከቆየ በኋላ ራሳቸውን ከቆዳቸው ጋር አስላጭቶ እሳት አነደደባቸው፡፡ ዳግመኛም ከትከሻቸው እስከ እግራቸው ድረስ በሚደርሱ ችንካሮች ቸነከራቸው፡፡ በዚህ ጊዜ የእግዚአብሔር መልአክ ቅዱስ ገብርኤል ከእግዚአብሔር ዘንድ ተልኮ ከሥቃያቸው አድኗቸዋል፡፡ አሁንም ቀኑን ሙሉ በልዩ ልዩ የሥቃይ መሣሪያዎች ቢያስጨንቃቸውም የእግዚአብሔር ኃይልና የቅዱስ ገብርኤል ተራዳኢነት አልተለያቸውም ነበርና ምንም ዓይነት ጉዳት አልደረሰባቸውም፡፡ እንደ ገናም በመጋዝ ሰንጥቀው በብረት ምጣድ በቆሏቸው ጊዜ ጌታችን ከሞት አነሣቸውና በመኰንኑ ፊት ድንቅ ተአምራትን አደረጉ፡፡ ከተአምራቱ መካከልም ሕፃኑ ቅዱስ ቂርቆስ የመኰንኑን ጫማ በጸሎት ወደ በሬነት እንዲቀየር ማድረጉ ተጠቃሽ ሲኾን፣ መኰንኑ በተአምራቱ ተቈጥቶ የቅዱስ ቂርቆስን ምላስ አስቈርጦታል፤ ጌታችንም ምላሱን አድኖለታል፡፡
ዳግመኛም በፈላ የጋን ውኀ ውስጥ ቅዱሳን ቂርቆስና ኢየሉጣን ሊጨምሯቸው ሲሉ ቅድስት ኢየሉጣ በፈራች ጊዜ ቅዱስ ቂርቆስ ‹‹እናቴ ሆይ አትፍሪ፤ አናንያ፣ ዓዛርያና ሚሳኤልን ከእሳት ነበልባል ያዳናቸው እግዚአብሔር እኛንም ከዚህ የፈላ ውኀ ያድነናል›› እያለ ያረጋጋትና በተጋድሎዋ እንድትጸና ወደ እግዚአብሔር ይጸልይላት ነበር፡፡ ከዚህ በኋላ ተያይዘው ወደ ጋኑ ውስጥ ገቡ፡፡ ያ ውኀም እንደ ውርጭ ቀዘቀዘ፡፡ ደግሞም ወታደሮቹ መንኰራኵር ባለበት የብረት ምጣድ ውስጥ አስገብተው ሥጋቸው እስኪቈራረጥ ድረስ በጎተቷቸው ጊዜ ቅዱስ ገብርኤል አድኗቸዋል፡፡ በመጨረሻም ከእግዚአብሔር ቃል ኪዳን ተቀብለው በመንፈቀ ሌሊት አንገታቸውን ተቈርጠው በሰማዕትነት ዐርፈዋል፡፡ እስከ ሞት ድረስ በታመኑበት ተጋድሏቸውም ከእግዚአብሔር ዘንድ የሕይወትን አክሊል ተቀብለዋል፡፡
በአጠቃላይ ቅዱስ ቂርቆስና ቅድስት ኢየሉጣ የዚህን ዓለም ጣዕም በመናቅ ‹‹ሞት ቢኾን፣ ሕይወትም ቢኾን፣ መላእክትም ቢኾኑ፣ ግዛትም ቢኾን፣ ያለውም ቢኾን፣ የሚመጣውም ቢኾን፣ ኃይላትም ቢኾኑ፣ ከፍታም ቢኾን፣ ዝቅታም ቢኾን፣ ልዩ ፍጥረትም ቢኾን በክርስቶስ ኢየሱስ በጌታችን ካለ ከእግዚአብሔር ፍቅር ሊለየን እንዳይችል ተረድቼአለሁ፤›› (ሮሜ. ፰፥፴፰-፴፱) በማለት ቅዱስ ጳውሎስ የተናገረውን ቃል በተግባር በማሳየት ለክርስቶስ ፍቅር ሲሉ ራሳቸውን ለመከራና ለሞት አሳልፈው ሰጥተዋል፡፡ ቅዱሳኑ ተጋድሏቸውን እስኪፈጽሙ ድረስም ቅዱስ ገብርኤል አልተለያቸውም፡፡ በቅዱስ ገብርኤል ተራዳኢነት ቅድስት ኢየሉጣና ቅዱስ ቂርቆስ ብቻ ሳይኾኑ ብዙ ምእመናንም ተጠቅመዋል፡፡ ስሙ በሚጠራባቸው ገዳማትና አድባራት መልአኩ የሚያደርጋቸው ድንቅ ድንቅ ተአምራት ለዚህ ማስረጃዎች ናቸው፡፡ ይህም ቅዱሳን መላእክት በእግዚአብሔር ስም መከራ የሚቀበሉ ምእመናንን እንደሚጠብቁና ከልዩ ልዩ ደዌ እንደሚፈውሱ የሚያስረዳ ታሪክ ነው፡፡
እኛም በሃይማኖታችን ምክንያት መከራ ባጋጠመን ጊዜ ቈራጥ ልብ ያለው ሕፃኑ ቅዱስ ቂርቆስ ‹‹እናቴ ሆይ አትፍሪ›› እያለ እናቱን በመከራ እንድትጸና እንዳረጋጋትና ለሰማዕትነት እንድትበቃ እንዳደረጋት ዅሉ፣ ዘለዓለማዊውን የእግዚአብሔርን መንግሥት በአንድነት ለመውረስ እንድንችል ‹‹አይዞህአይዞሽአትፍራአትፍሪ›› በመባባል በዚህ ዓለም የሚገጥመንን መከራ ታግሠን፣ እስከ ሞት ድረስ በሃይማኖታችን ጸንተን መኖር ይገባናል፡፡ ክርስትና ለብቻ የሚጸደቅበት መንገድ ሳይኾን በጋራ ዋጋ የሚያገኙበት የድኅነት በር ነውና፡፡ ከዚሁ ዅሉ ጋርም ቅዱስ ቂርቆስንና ቅድስት ኢየሉጣን የተራዳው የእግዚአብሔር መልአክ ቅዱስ ገብርኤል በአማላጅነቱ እንዲጠብቀን ‹‹በተአምኖ ንሴፎ ትንባሌ ዚአከ መዓልተ ወሌሊተ፤ በእግዚአብሔር ታምነን በቀንም በሌሊትም የአንተን ልመና ተስፋ እናደርጋለን›› እያልን ዘወትር ልንማጸነው ያስፈልጋል፡፡ እርሱ ከፈጣሪው ከእግዚአብሔር በተሰጠው ቃል ኪዳን መሠረት ከሚደርስብን ልዩ ልዩ መከራና ሥቃይ ያድነናልና፡፡ ‹‹የእግዚአብሔር መልአክ በሚፈሩት ሰዎች ዙርያ ይሠፍራል፤ ያድናቸውማል፤›› ተብሎ እንደ ተጻፈ (መዝ. ፴፬፥፯)፡፡ ይህን እንድናደርግም የቅዱሳን ተራዳኢነት አይለየን፡፡ የቅዱስ ገብርኤል፣ ቅድስት ኢየሉጣ እና ቅዱስ ቂርቆስ ጸሎታቸው፣ ምልጃቸው ይጠብቀን፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር


Thursday, December 19, 2019

እሪዮ / ምሽግ

እሪዮ / ምሽግ

በአንድራቻ ወረዳ፤ ጨገቻ ቀበሌ፤ ከወረዳው ዋና ከተማ ጌጫ በ7ኪሜ ርቀት ላይ ይገኛል፤
የሸካ ንጉስ ግባጋዮች ዘመን ጠላት ሲመጣ  /ጎነኮሶ/ ጠላት መምጣቱን ለማሰማት ጥሪ ያስተላልፋሉ፤
ጠላት ቀጥታ ሲመጣ በተቆፈረው ምሽግ /እርዮ/ ውስጥ እንዲገባ መንገዱን ጠርገው ያስተካክላሉ፤ ከዚያም በኋላ ፈረሰኞች ጋሻና ጦር ይዘው እየጋለቡ ሄደው በተቆፈረው ጉድጓድ ዉስጥ ሰምጠው ይቀራሉ፤ ጉድጓዱ በግምት ጥልቀቱ ከ5-6 ሜትር የሚሆን ሲሆን የተለያዩ ስለት ያላቸው ቁሳቁሶችን ከቸከሉ በኋላ ጠላት ገብቶ የሚማረክበት ሂደት እንደነበረ የታሪክ አዋቂዎች ይናገራሉ፡፡

ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ከ100 ተፅዕኖ ፈጣሪ ሴቶች አንዷ ሆኑ

ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ከ100 ተፅዕኖ ፈጣሪ ሴቶች አንዷ ሆኑ

ፎርብስ መጽሔት ፕሬዚዳንት ሳህለ ወርቅ ዘውዴን ከ100 የዓመቱ ተፅዕኖ ፈጣሪ ሴቶች መካከል መርጧቸዋል፡፡ ፕሬዚዳንቷ ከመቶ የዓመቱ ተፅዕኖ ፈጣሪ ሴቶች መካከል የተመረጡ ብቸኛ አፍሪካዊት ናቸው፡፡ ፎርብስ ካወዳደራቸው ሴቶች መካከልም ፕሬዚዳንት ሳህለ ወርቅ 93ኛ ደረጃን ይዘዋል፡፡
ዓምና ጥቅምት ወር ላይ የመጀመርያ ሴት ፕሬዚዳንት ሆነው የተመረጡት ፕሬዚዳንት ሳህለ ወርቅ፣ አገራቸውን በዲፕሎማሲው ዘርፍ ለረዥም መታት ያገለገሉ ናቸው፡፡ በተለያዩ ዓለም አቀፍ ድርጅቶችም በልዩ ልዩ ኃላፊነት ደረጃዎች ሠርተዋል፡፡
አምና ከተመረጡ ተፅዕኖ ፈጣሪ ሴቶች መካከል አፍሪካዊቷ ኢሳቤላ ዶ ሳንቶስ አንዷ ነበሩ፡፡ ኢሳቤላ የቀድሞ የአንጎላ ፕሬዚዳንት ሆዜ ኤድዋርዶ ዶ ሳንቶስ ልጅ እንደሆኑ ፎርብስ አስታውሷል፡፡
የጀርመኗ አንጌላ መርኬል፣ ከፈረንሣይ ክርስቲን ላጋርዴ፣ ከአሜሪካ ናንሲ ፔሎሲ በዓመቱ ተፅዕኖ ፈጣሪ ሴቶች ዝርዝር ውስጥ ቀዳሚ በመሆን ከአንድ እስከ ሦስተኛ ደረጃ ይዘዋል፡፡ ሜሊንዳ ጌትስ ስድስተኛ፣ ኦፕራ ዊንፍሬይ 20ኛ ሆነው ሲመረጡ፣ የአየር ንብረት ጥበቃ ተሟጋቿ የ16 ዓመቷ ታዳጊ ግሬታ ተንበርግ ደግሞ 100ኛ ሆናለች፡፡