Saturday, September 25, 2021

የመስቀል በዓል ታሪካዊ አመጣጥ

የመስቀል በአል ታሪካዊ አመጣጥ 


የመስቀል በዓል ስናከብር ልናጤነው የሚገባን ዐቢይ ቁም ነገር አይሁድ ክርስቶስ የተሰቀለበትን መስቀል ቆሻሻ ማጠራቀሚያ ቦታ በመቅበር እንዲረሳ ለማድረግ ቢሞክሩም በንግሥት ዕሌኒ አማካኝነት እንዴት እንደተገኘና የቀኝ እጁ የተቸነከረበት ክፋይ ወይም ግማድ እንዴት ወደ ሀገራችን እንደመጣ እንቃኛለን፡፡ መልካም የመስቀል በዓል ይሁንላችሁ!

የመስቀል በዓል ታሪካዊ አመጣጥ

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሰው ልጆችን ለማዳን የተሰቀለበት ቅዱስ መስቀል ሕሙማንን በመፈወሱ ምክንያት በርካታ አሕዛብ ክርስቲያን እንዲሆኑ አስችሏል፡፡ በተአምራዊነቱና በክርስቲያኖች ዘንድ ከፍተኛ ክብር የተሰጠው በመሆኑና ይህን የተመለከቱ አይሁድ ቅዱስ መስቀሉን በአንድ የቆሻሻ ማጠራቀሚያ ቦታ እንዲቀበር አደረጉ፡፡ የአካባቢው ነዋሪዎች በየቀኑ ቆሻሻ ስለሚጥሉበት ቦታው ወደ ተራራነት ተቀየረ፡፡ ምንም እንኳን መስቀሉን ለማውጣት ባይችሉም በኢየሩሳሌም የነበሩ ክርስቲያኖች ቦታውን ያውቁት ነበር፡፡ በሰባ ዓመተ ምሕረት በጥጦስ ወረራ ኢየሩሳሌም ስለጠፋች በዚያ የነበሩ ክርስቲያኖች ተሰደዱ፡፡ የተቀበረበትን ቦታ የሚያውቅ ባለመገኘቱ መስቀሉ ከ300 ዓመታት በላይ ተዳፍኖ /ተቀብሮ/ ኖረ፡፡

በ326 ዓ.ም. የንጉሥ ቆስጠንጢኖስ እናት ንግሥት ዕሌኒ ቅዱስ መስቀሉን ለመፈለግ ወደ ኢየሩሳሌም ጉዞ አደረገች፡፡ እዚያም ደርሳ ጉብታ የሆነውን ሁሉ ብታስቆፍር መስቀሉ ያለበትን ቦታ ማግኘት አልቻለችም፤ ሰውም ብትጠይቅ የሚያውቅ አልተገኘም፡፡ በመጨረሻም የመስቀሉ መገኘት የእግዚአብሔር ፈቀድ ነበርና አንድ ይሁድ አረጋዊ የታሪክ አዋቂና ሽማግሌ አግኝታ ቅዱስ መስቀሉ የተቀበረበትንና የተጣለበትን አካባቢ ያውቅ ዘንድ ጠየቀችው፡፡ ሽማግሌውም “አንቺም በከንቱ አትድከሚ ሰውንም አታድክሚ እንጨት አሰብስበሽ እጣን አፍሽበት በእሳትም አያይዢው የእጣኑ ጢስ ወደላይ ወጥቶ ወደታች ሲመለስ አቅጣጫውን አይተሽ አስቆፍሪው በዚህ ምልክት ታገኚዋለሽ” አላት እርሷም ያላትን ሁሉ አደረገች። እንጨት ደምራ በዚያ ላይም ዕጣን ጨምራ በእሳት ለኮሰችው፤ የዕጣኑ ጢስ ወደ ላይ ወጥቶ ወደ ታች ሲመለስ መስቀሉ ያለበትን ቦታ በጣት ጠቅሶ እንደማሳየት ያህል አመለከተ፡፡ ንግሥት ዕሌኒም ጢሱ ያረፈበት ቦታ ቅዱስ መስቀሉ የተቀበረበት እንደሆነ አመነች፡፡ ይህ ይሁድ አረጋዊ የታሪክ አዋቂና ሽማግሌ በኋላ በክርስቶስ አምኖ ተጠምቋል፤ ስሙም ኪርያኮስ ተብሏል፡፡

በዚህም መሠረት ከመስከረም 17 ቀን አስጀምራ እስከ መጋቢት 10 ቀን ሌሊትና ቀን ለሰባት ወራት ያህል የጉድፍን ኮረብታ ቆፍረው ቆሻሻውንም ካስወገዱ በኋላ ሦስት መስቀሎች ተገኙ ፡፡ የጌታም መስቀል ሙት በማስነሣቱ ተለይቶ ታውቋል፡፡ መስቀሉ የተገኘው መጋቢት 10 ቀን 326 ዓ.ም. ነበር፡፡ ቅድስት ዕሌኒ ይህን ተአምር በማየቷ እጅግ ደስ አላት፡፡ ሕዝቡም ሁሉ መስቀሉን እየዳሰሱ ኪርያላይሶን እያሉም በመዘመር ደስታና ሐሴት አደረጉ፡፡ ቀኑ መሽቶ ጨለማ በሆነ ጊዜም የኢየሩሳሌም ጳጳስ ብፁዕ አቡነ መቃርዮስና ንግሥት ዕሌኒ፣ ሠራዊቱና ሕዝቡ በሰልፍ በችቦ መብራት መዝሙር እየዘመሩ ቅዱስ መስቀሉን ወደ ቤተ ክርስቲያን ወስደው በአንድ የጸሎት ቤት አኖሩት፡፡ በኋላም በንጉሥ ቆስጠንጢኖስ ዕብነ መሠረት ወይም የመሠረት ድንጋይ ተቀምጦ ለመሰቀሉ መታሰቢያ ቤተክርስቲያን ተሠርቶ ተመርቆ የገባው (ቅዳሴ ቤቱ) የተከበረው መስከረም 17 ቀን 327 ዓ.ም. ነው፡፡ በቤተ ክርስቲያናችን ሁለቱም ዕለታት ይከበራሉ፤ በደማቅ ሁኔታና በመጀመሪያ ደረጃ የሚከበረው ግን መስከረም 17 ነው፡፡ ይህም የሆነበት ምክንያት መጋቢት 10 ቀን ሁልጊዜም በዐቢይ ጾም ወቅት የሚውል መሆኑና ለመስቀሉ የተሠራው ቤተ መቅደስ የተከበረው መስከረም 17 በመሆኑ ነው፡፡

ይህ ዕለት ከ300 ዓመታት በላይ ጠፍቶ የነበረውን ቅዱስ መስቀል በንግሥት ዕሌኒ አማካኝነት መገኘቱን የምንዘክርበት በዚህም ደስ የምንሰኝበት ዕለት ነው፡፡ ይህን መነሻ በማድረግ በኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ደመራ በመደመር የመስቀል በዓል በታላቅ መንፈሳዊ ሥነ ሥርዐት ይከበራል፡፡


የደመራ ትርጉም

ደመራ የሚለው ቃል – ደመረ፣ ጨመረ፣ አንድ አደረገ፤ ከሚለው የግእዝ ቃል የተወረሰ ሲሆን መቀላቀልን፣ መገናኘትን፣ መሰብሰብን፣ መጣመርን፣ መዋሐድን በአጠቃላይ ሱታፌን፣ አንድነትን እና ኅብረትን ያመለክታል፡፡ ቅዱስ መስቀሉ በተገኘበት ቦታም ስለሆነም ደመራ እንጨቶች የሚደመሩበት የበዓለ መስቀል ዋዜማ ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያናችን ከምታከብራቸው ዘጠኙ የጌታችን ንዑሳን በዓላት አንዱ በዓል ነው፡፡ መስቀል የሰላማችንና የድኅነታችን የመቀደሳችን ዓርማ፣ ኢየሱስ ክርስቶስ የሰውን ልጆች ለማዳን፥ የዘላለም ሕይወትን ለመስጠት መስዋዕትነት የከፈለበት ቅዱስ ሥጋውን ክቡር ደሙን ያፈሰሰበት መንበር፥ ሲሆን አምላካችንን የምንመለከትበት መስታወት ነው።


በሀገራችን በኢትዮጵያ የመስቀልን በዓል ደመራ በመደመርና ችቦ በማብራት፥ ቅዳሴ በመቀደስና ማኅሌት በመቆም የምናከብረው ለዚህ ነው። በዚሁም ላይ ይህን ታላቅ ዕፀ መስቀል በወቅቱ የነበሩ ታላላቅ ነገሥታት የሚያደርጋቸውን ተዓምራት በማየት ለእያንዳንዳቸው ይደርሳቸው ዘንድ ከአራት ክፍል ሲከፍሉት ከአራቱ አንዱ የቀኝ እጁ ያረፈበት ግማድ /ክፋይ/ ብቻ በደብረ ከርቤ ግሸን ማርያም ሲገኝ ሌሎች ሦስቱ ግን የት እንደደረሱ አይታወቅም።


መስቀሉ እንዴት ወደ ሀገራችን መጣ?

የጌታችን ቅዱስ መስቀል ወደ ሀገራችን ሊመጣ የቻለበት 1394 ዓ.ም. ሁለተኛ በነገሡ በ29ኛ ዓመታቸው የእስክንድርያ ቤተ ክርስቲያን ሊቀጳጳስ ብፁዕ አቡነ ሚካኤል 47ኛ በወቅቱ የነበረው የግብጽ ፈርዖን አሠራቸው ክርስቲያን የሆኑ ዜጎቹን “የእኔን ሃይማኖት ካልተከተላችሁ በግብጽ መኖር አትችሉም” ብሎ ከአቅማቸው በላይ ግብር ጣለባቸው፡፡ መከራው የጸናባቸው የግብጽ ክርስቲያኖች “ከደረሰብን መከራና ሊቀጳጳሳችንን ታስፈታልን ዘንድ በእግዚአብሔር ስም ተማጽነናል” ሲሉ ለአፄ ዳዊት መልእክት ላኩባቸው፡፡
አፄ ዳዊት “ክተት ሠራዊት ምታ ነጋሪት” ብለው አዋጅ በማወጅ ጦርነት ለማካሔድ ወስነው ወደ ካርቱም ጦራቸውን አዘመቱ፡፡ ካርቱም ደርሰው ሁኔታውን ሲያዩ ጦርነት ከማካሔድ ለምን የዐባይን ወንዝ አልገድብም ብለው ወሰኑ፡፡ ይህንንም ተግባራዊ ለማድረግ እንቅስቃሴ ማድረግ ጀመሩ፡፡ ይህን የሰሙ የወቅቱ የግብጽ መሪ መርዋን እልጋዴን መኳንቱን ሰብስበው “ምን ይሻለናል ብለው ምክር ያዙ” የዐባይን ወንዝ ከምናጣ “ሊቀጳጳሱን አቡነ ሚካኤልን እንፈታለን በክርስቲያኖችም ላይ መከራ አናደርስም” ብለው ቃል በመግባት ብፁዕ አቡነ ሚካኤልን ሁለት እልፍ ወቂት ወርቅ እጅ መንሻ አስይዘው ለዐፄ ዳዊት አማላጅ ላኩ፡፡
ንጉሡ ዐፄ ዳዊትም “ብርና ወርቅ አልፈልግም ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ የተሰቀለበትን መስቀል ነው የምፈልገው” አሏቸው፡፡ የሀገራችን ሕዝብ በውኃ ጥም ከሚያልቅ ብንስማማ ይሻለናል ብለው መስከረም 10 ቀን 1395 ዓ.ም. ከመስቀሉ ጋር ቅዱስ ሉቃስ የሳላት የእመቤታችን ሥዕል ጨምረው ሰጧቸው፡፡ በየዓመቱ መስከረም 10 ቀን የተቀጸል ጽጌ /የዐፄ መስቀል/ እየተባለ የሚከበረው ይህን መነሻ በማድረግ ነው፡፡
የታላቋን ንግሥት ዕሌኒን ታሪክ በማስታወስ መስከረም 17 የመስቀል በዓልን ካከበሩ በኋላ “መስቀልየ ይነብር በዲበ መስቀል /መስቀሌ በመስቀል ላይ ይኖራል/” የሚል ራእይ ታያቸው፡፡ “ይሔ ነገር ምሥጢሩ ምንድን ነው?” እያሉ በድንገት ሲናር ላይ አርፈው አጽማቸው ዳጋ እስጢፋኖስ አርፏል፡፡


በእሳቸው እግር የተተኩት ልጃቸው ዐፄ ዘርዓ ያዕቆብ “አንብር መስቀልየ በዲበ መስቀል /መስቀሌን በመስቀልያ ስፍራ አስቀምጥ/” የሚል ራእይ በተደጋጋሚ እግዚአብሔር አሳያቸው፡፡ በኢትዮጵያ ካሉት መልከዐ ምድር ውስጥ የመስቀል ቅርጽ ያለው የቀራንዮ አምሳል የሆነ ቦታ ከፈለጉና ካጠኑ በኋላ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶሰ በቀራንዮ የተሰቀለበት ቀኝ እጁ ያረፈበት ግማደ መስቀል አሁን ግሼ አምባ በሚባለው ሥፍራ ላይ መስከረም 21 ቀን 1446 ዓ.ም ደብረ ከርቤ አሁን እግዚአብሔር አብ ቤተ ክርስቲያን የታነጸበት ቦታ ላይ እንዲያርፍ አደረጉ፡፡



ግሸን ደብረ ከርቤ ማርያም ገዳም 

የግሸን ደብረ ከርቤ ማርያም ገዳም ወሎ ክፍለ ሃገር፣ አምባሰል ወረዳ ውስጥ ግሸን ተራራ አናት ላይ የምትገኝ ቤተ ክርስቲያን ናት። ለዚች ቤተ ክርስቲያን መግቢያ አንድ መንገድ ብቻ ነው። እንደ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ትውፊት ይህች ቤተ ክርስቲያን በየዘመኑ የተለያየ ስያሜን አግኝታለች።

የግሸን ደብረ ከርቤ ማርያም ገዳም መጠሪያ ስሞች

ግሸን ደብረ ከርቤ ማርያም ገዳም መጠሪያ ስሞች በተለያዩ ዘመናት የተለያዩ እንደነበር የታሪክ ድርሳናት ይነግሩናል፡፡
 ከዐፄ ድልናኦድ ዘመን /866 ዓ.ም/ እስከ 11ኛው ክፍለ ዘመን በአሁኑ ስያሜ /ደብረ ከርቤ/ ትታወቅ ነበር።
• በ11ኛው ክፍለ ዘመን አጼ ላሊበላ ከቋጥኝ ድንጋይ ፈልፍለው እግዚአብሔር አብ የተሰኘ ቤተ ክርስቲያን በዚሁ ቦታ ሲያሰሩ ደብረ እግዚአብሔር በሚል ስም ታወቀች። ብዙ ሳይቆይ ግን ደብረ ነገሥት ተባለች።
• በ1446 ዐፄ ዘርዓ ያዕቆብ ግማደ መስቀሉ በዚህ ስፍራ ሲያርፍ ደብረ ነገሥት መባሏ ቀርቶ ደብረ ከርቤ ተባለች።
ዐፄ ዘርዓ ያዕቆብ ግማደ መስቀሉን ይዘው እየገሰገስገሱ ስለመጡ በግዕዙ “ገሰ” ወይም በአማርኛው “ገሰገሰ” የሚለው ቃል ለቦታው ስያሜ ሆነ። በዘመናት ሂደት ገስ ወደ ግሸን የሚለው ስያሜ ተቀየረ። አካባቢው በዚህ ስም እንደተጠራ የግሸን ደብረ ከርቤ ገዳም ታሪክ የጻፉት የመሪጌታ የማነ ብርሃን አዲሴ መጽሐፍ በስፋት ይነግረናል፡፡ የግሸን ደብረ ከርቤ ገዳም ታሪክ በስፋት ለማወቅ የምትፈልጉ ወገኖቻችን መጽሐፋቸውን ብታነቡ ተጨማሪ መረጃ ማግኘት ትችላላችሁ እያልን በዚሁ እንሰናበት፡፡ 

በቸር ያገናኘን!

Sharing is caring

Tuesday, September 7, 2021

ሎጊታና ገላና የሲዳማ ጸጋዎች፤ የኢትዮጵያ አዲስ ሀብቶች

 ሎጊታና ገላና የሲዳማ ጸጋዎች፤ የኢትዮጵያ አዲስ ሀብቶች 


(ተጓዡ ጋዜጠኛ ሄኖክ ስዩም ሲዳማ ክልል ስደርስ ድባቡ ሁሉ የእናት ሀገር ጉዳይ ነው፡፡ የሲዳማ ልቡ ሰሜን ኢትዮጵያ ዘልቋል፡፡ መንደሮቹ ለሀገር መከላከያ ሠራዊት ደጀን ለመሆን ያላቸውን ይለግሳሉ፤ ከተሞቹ ወኔ ቀስቃሽ ናቸው ሲል እስከ ሎጊታና ገላና ፏፏቴዎች ያደረገውን ጉዞ እንዲህ ያጋራናል፡፡)



(ሄኖክ ስዩም -ድሬ ቲዩብ)

ሲዳማ ነኝ፡፡ የገባሁበት ሁሉ በሀገር ጉዳይ መንፈስ ታውዷል፡፡ የሲዳማ ልቡ ሰሜን ላይ ነው፡፡ የእናት ሀገሩን ውሎ ያደምጣል፡፡ ብዙ ቦታዎች ስለ ሀገር ፍቅር፣ ስለጁንታው መደምሰስ የሚገልጹ ጽሑፎችን አይቻለሁ፡፡

ከሀዋሳ ደቡብ ምስራቅ አቅጣጫ 119 ኪሎ ሜትር ተጉዤ የደርስኩበት ይህ ስፍራ የሲዳማ ሌላ ውበት በድንቅ የፏፏቴ ዜማ የሚደመጥበት ቀዬ ነው፡፡ አዲሱ ክልል በነባሩ የሀገራችን የቱሪዝም ልማት ላይ ብዙ ድብቅ ገጸ በረከቶችን ይዞ የመጣ ነው፡፡ አንዱ ጋር ደርሻለሁ፡፡

ቦና ወረዳ ይባላል፡፡ እዚህ አስደናቂዎቹ መስህቦች ይታያሉ፡፡ አሁን እኔ ሎጊታ ስር ቆሜያለሁ፡፡ ሎጊታ ከአርቤጎና ምድር ከጋራምባ ተራራ የሚመጣ ወንዝ ነው፡፡ እንዲህ ያለ ቦታ ሆኖ የሚታየውን ተአምርና አስደናቂ ሁኔታ የትም የለም፡፡

አካባቢው ውብ ነው፡፡ የሎጊታ ወንዝ ድንቅ መልከዓ ምድር ፈጥሯል፡፡ አካባቢው ውብና ለመንገድ ቅርብ ነው፡፡ ያቆሙትን መኪና በርቀት እያዩ የሚጎበኙት ፏፏቴ መሆኑ ከሀገሬ ፏፏቴ ልዩ ያደርገዋል፡፡

የሎጊታን ወንዝ ጉዞ ተከትዬ ሌላ ስፍራ ደረስኩ፡፡ ጋላና ወንዝ ደግሞ ሌላ ፏፏቴ ሰርቷል፡፡ አንድ ጊቢ ሁለት የታላላቅ ወንዝ ፏፏቴዎች አንዱ ጋር ሲደርሱ የሌላው ድምጽ እየሸኘ ውበት የሚታይበት፡፡

እነኚህ ሁለት ወንዞች ከፏፏቴዎቻቸው ግርጌ አንድ ሆነው ይዋህዳሉ፡፡ የሚዋህዱበት አፋፍ ቆሜ አየሁ፡፡ ጋላና እና ሎጊታ ስማቸው ከዚህ በኋላ አንድ ነው፡፡ ገናሌን ፈጥረዋል፡፡ ገናሌ ከጋራምባ መሀጸን ብዙ ምንጭ ሆኖ በተበተነ ውበት ሁለት ወንዝና ፏፏቴ ሆኖ በአንድ ስም ለመጠራት አንድ ወንዝ የሚሆንበት ስፍራ፤

ገናሌ ተጓዥ ወንዝ ነው፡፡ መንገደኛነቱን ከሚያሳዩን መረጃዎች አንዱ 858 ኪሎ ሜትሮችን የሚፈስ መሆኑ ነው፡፡ ከዚያ ውስጥ በእናት ሀገር ምድሩ 480 ኪሎ ሜትሮችን ይጓዛል፡፡ እነሆ እዚህ አንድ ብሎ እና ገናሌ ተብሎ ከሎጊታና ከገላና ወንዞች ተዳቅሎ ሲፈጠር እያየሁ ነው፡፡

የቀድሞዎቹ የባሌና ሲዳሞ ጠቅላይ ግዛቶች ድንበር የዛሬው የገናሌ ዳዋ ሃይል ማመንጫ ሀብት የሚፈጠርበት ቆሞ እንዲህ ማሰብ ደስ ያሰኛል፡፡

ወልመልና ወይብን ተቀላቅሎ ወደ ጁባ የሚገባው ወንዝ ምንኛ ደጋ ምድር ፈጠረው ብዬ ሌላ ስፍራ ለማየት ጓጓሁ፡፡ እናም ወደ ሲዳማ ደጋ ምድር ለመውጣትና የአርቤጎናን ምንጮች ለመመልከት ልጓዝ ነው፡፡

ግቢውን ለቅቄ ስወጣ ይከተለኝ የነበረው የጋላና ፏፏቴ ድምጽ ለሎጊታ ፏፏቴ አቀብሎኝ እስከ አስፋልቱ ጎዳና ሸኘኝ፡፡

አሁን አብረን ደጋማው የሲዳማ ምድር እንጓዛለን፡፡ በረደኝ የለም በሻፌታ ይቀርባል፡፡ የእርጎ ሀገር ነው፡፡ ንጹህ ቅቤ የሚገኝበት፡፡ የሲዳማ ጎጆ ለእንግዳ ቸር ነው፡፡ ያንን ለማየት እነዚህ መንደሮች መግባት ይጠይቃል፡፡


https://news.et/2021/09/03/%e1%88%8e%e1%8c%8a%e1%89%b3%e1%8a%93-%e1%8c%88%e1%88%8b%e1%8a%93-%e1%8b%a8%e1%88%b2%e1%8b%b3%e1%88%9b-%e1%8c%b8%e1%8c%8b%e1%8b%8e%e1%89%bd%e1%8d%a4-%e1%8b%a8%e1%8a%a2%e1%89%b5%e1%8b%ae%e1%8c%b5/

Sunday, January 19, 2020

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ለጥምቀት ያስተላለፉት መልእክት ሙሉ ቃል

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ለጥምቀት ያስተላለፉት መልእክት ሙሉ ቃል



"ለመላ የክርስትና እምነት ተከታይ ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ በሙሉ እንኳን ለብርሃነ ጥምቀቱ በሰላም አደረሳችሁ!"



በሀገራችን በድምቀት ከሚከበሩትና ኅብረ ብሔራዊ አንድነታችንን ከሚያሳዩት በዓሎቻችን ውስጥ አንዱ የጥምቀት በዓል ነው፡፡
ቀደምት አባቶቻችን እና እናቶቻችን ይህንን በዓል እንድናከብር ሥርዓት ሲሠሩ በአንድ በኩል በትህትና ስለ ዝቅ ማለት እና ስለ መለወጥ፣ በሌላም በኩል ደግሞ ስለ መደመር ሊያስተምሩን የፈለጉ ይመስለኛል፡፡ የቃና ዘገሊላን በዓል ያስከተሉትም መለወጥ ምን ማለት እንደሆነ ይበልጥ እንድንረዳው ነው፡፡
ኢየሱስ ክርስቶስ ዘጠና ዘጠኙን ነገደ መላእክት ትቶ በባሕር መካከል ተገኘ እንላለን፡፡ ዝቅ ያለው ከፍ ሊያደርገን፣
የወረደውም ሊያወጣን ነው፡፡ ሕዝባችን ወደ ሥልጣኔ ሠገነት ከፍ እንዲል ከፈለግን፣ እኛ ዝቅ ማለት አለብን፡፡
መውረድ አለብን፡፡ ሳይወርዱ መውጣት፣ ዝቅ ሳይሉ ከፍ ማድረግ ፈጽሞ አይታሰብም፡፡ እርሱ በመንበሩ ሆኖ ‹ኑ› አላለንም፡፡ እንደማንችል ያውቃልና ወደኛ መጣ፡፡ ሕዝቡን ይህንን አድርግ፣ ይህንን ሥራ፣ እንዲህና እንዲያሁን ማለት ለውጥ አያመጣም፡፡ ይልቅስ ወደ ሕዝቡ እንውረድ፡፡ ችግሩን እንቅመስለት፣ መከራውን እንይለት፣ ተሸከርካሪ ወንበሮቻችንን፣ ያማሩ ቢሮዎቻችንን ትተን ወደ ታች- ወደ ችግሩ ዝቅ እንበል፡፡
ሐኪሙ ወደ ሕመምተኞች፣ ባለ ሥልጣኑና ባለ ሞያው ወደ ባለ ጉዳዮች፣ ሥራ አስኪያጁ ወደ ተራዎቹ ሠራተኞች፣ መምህሩ ወደ ተማሪዎች፣ በአጠቃላይም አገልጋዩ ወደ ተገልጋዮች እንውረድ፡፡ ሕዝቡን ወደ እኛ ውጣ አንበለው፡፡ ክርስቶስ ወደ ባሕሩ ሰው ፍለጋ ሲወርድ መላእክቱም አብረውት ወረዱ፡፡ እኛ መውረድ ከጀመርን ሌሎችም ተከትለው ወደ ሕዝቡ ይወርዳሉ፡፡ የሕዝቡንም ችግር ያያሉ፡፡ አይተውም ይፈታሉ፡፡ አስቀድሞ የሕዝብን ችግር ለመፍታት ወደ ሕዝብ መውረድ የለመደ ኑሮውም ሕይውቱም የሕዝቡ ነውና በኋላ ከሥልጣኑ ሲወርድ አይጨንቀውም- አይጠበውም፡፡ በፊትም ቢሆን ወደ ሕዝብ የወረደ እና ውክልናውም ሆነ ውግንናው ከህዝብ ነውና የመውረድ ኑሮ ግር አይለውም፡፡
ይህ በዓል የመለወጥ በዓል ነው ብለናል፡፡ ከተለወጡት ውስጥም አንዱ ውኃ ነው፡፡ የሰው ልጅ ከውሀው መለወጥ
በፊት በነበረው ታሪኩ ውኃን የሚያስታውሰው በቁጣ መሣሪያነቱ ነው፡፡ የሰው ልጅ በውኃ ጠፍቷል፡፡ አሁን ግን
ክርስቶስ ወደ ውኃው መጣ፡፡ የመዓቱን ውኃ የምሕረት አደረገው፡፡ በሀገራችንም ሕዝባችን በክፉ ሚያስታውሳቸው አያሌ ሞያዎችና ተቋማት አሉ፡፡ በቢሮክራሲያቸው፣ በግፋቸው፣ በማሰቃያነታቸው፣ በሰብአዊ መብት ጥሰታቸው፣ በአሳዳጅነታቸው፣ በኢፍትሐዊነታቸው፣ በአድሏዊነታቸው፣ ለተወሰኑ አካላት ጥቅም በመቆማቸው የተነሣ በመዓት የምናስታውሳቸው ተቋማት አሉን፡፡ አሁን የሚሻለን ምርጫ አልባ ምርጫ እነዚህን የክፋት መታወሻዎች እንደ ውኃው ሁሉ ወደ በረከትነት መቀየር ነው፡፡ ለመዓት የነበረው ውኃ ለምሕረት እንደተለወጠው ሁሉ በክፉ ሥራቸው የምናስታውሳቸውን ተቋሞቻችንንም ለሕዝብ የሚጠቅም ሥራ እንዲሠሩ አድርገን እንለውጣቸው፡፡ ሕጋቸውን፣ አሠራራቸውን፣ አደረጃጀታቸውን፣ ዕሴቶቻቸውን፣ አስተሳሰባቸውንና አካሄዳቸውን ሁሉ ለፍትህ እና ለእኩልነት ወደ ወገነ መልክ እንለውጣቸው፡፡
ክርስቶስ ከመንገድ ጠርጎ ያስወገደው ነገር አለ፡፡ ለውጦ እንድንጠቀምበት ያደረገውም አለ፡፡ እኛም ከመንገዳችን ማስወገድ ያለብን ነገር አለ፡፡ ፈጽሞ እንዳንሄድ፣ ነጻ እንዳንወጣ፣ አንገታችንን እንድንደፋ፣ ቅስማችን እንዲሰበርና መንፈሳችን እንዲታወክ ያደረገውን ነገር ከመንገዳችን ገለል እናደርገዋለን፡፡ እርሱ የማይለወጥ ነው፡፡ የማይለወጥን ነገር ለመለወጥ መነሣት ነፋስን እንደሚከተል ሰው ትርፉ ድካም ነው፡፡ ግን ደግሞ ሁሉን አስወግደን አንዘልቀውም፡ በምሬታችን፣ በቁጣችን፣ በደረሰብን ግፍና መከራ ልክ ሁሉንም እናስወግድ ካልን የሚተርፈን አንዳች ነገር የለምና ሀገር ባዶዋን ትቀራለች፡፡ የተዋረደች ሀገር ከፍ እንድትል ማስወገድ ያለብን ነገር የመኖሩን ያህል መለወጥ ያለብንም ብዙ ነገር አለ፡፡ ውኃውን ሁሉ ማፍሰስ የለብንም፤ አንዳንዱን ወደ ወይን ጠጅነት እንዲቀየር ማድረግም ከሰሞነ ጥምቀት ልንወርሳቸው ከሚገቡን ቁም ነገሮች ውስጥ አንዱ ነው፡፡
በዚህ ቀን አንድ ታላቅ ሰው እናስታውሳለን፤ መጥምቁ ዮሐንስ፡፡ እውነተኛ፤ ቆራጥ፣ ፊት አይቶ የማያደላ፣ ሰው እንዲለወጥ እንጂ እንዲጠፋ የማይፈልግ፣ ለድኾች ጥብቅና የሚቆም ሰው ነው – ዮሐንስ፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ዮሐንስ ከመምጣቱ በፊት ብዙ ሰዎች ቀድመው መጥተው ነበር፡፡ ዮሐንስ በዚያ በረሐ ሦስት ነገሮችን ያደርግ ነበር፡፡ የሚመጡ ሰዎች ሲጠይቁት የሚገባቸውን ይነግራቸዋል፡፡ ምንን መለወጥ እንዳለባቸው ይመክራቸዋል፡፡ ቀጥሎም ካልተለወጡ ምን እንደሚያጋጥማቸው ያስጠነቅቃቸዋል፡፡ ከዚያም ዋና ተልዕኮው የሆነውን ማጥመቁን ይቀጥላል፡፡ መጥምቁ ዮሐንስ በዋናው ተልዕኮው ላይ ሲያተኩር እንጂ ጊዜውን ከመጡት ሰዎች ጋር በመጨቃጨቅና እነርሱንም ለማሳመን በመጣጣር ሲያጠፋ አናየውም፡፡ ለእርሱ ዋናው ጉዳይ ተልዕኮውን መፈጸሙ ነው፡፡
በዓላማው ላይ ያተኩራል እንጂ ሰዎች በሚፈጥሩለት አጀንዳ ውስጥ ገብቶ ዘይት እንደሚጨምቅ ግመል አታካች አዙሪት ውስጥ አይኳትንም፡፡ ፈሪሳውያንና ሰዱቃውያን መጥተው ነበር፡፡ ቀራጮች ወይም ግብር ሰብሳቢዎችም መጥተው ነበር፡፡ ወታደሮችም መጥተው ነበር፡፡ ለሁሉም የሚገባቸውንና ማሻሻል ያለባቸውን ነገራቸው፡፡ ከዚያም ወደ ዋናው ተልዕኮ ገባ፡፡
የኛም የለውጥ ጉዞ መርሕ ይህ መሆን አለበት፡፡ ጉልበታችንን፣ ጊዜያችንን፣ ገንዘባችንን እና ልምድ እውቀታችታችንን በዋነኝነት ማዋል ያለብን ዋናው የለውጣችን ተልዕኮ ላይ ነው፡፡ በጎዳናችን ከሚያጋጥሙን
አይለወጤዎች ጋር ሁሉ ስንከራከር፣ ስንጨቃጨቅ፣ መልስ ስንሰጥና እነርሱን እናሳምናለን ብለን ስንደክም አንውልም፡፡ እንዲለወጡ እንንገራቸው፤ መንገድ እናሳያቸው፤ ቅን ልብ ይዘን እንቅረባቸው፡፡ ከዚያ በኋላ ያለውን ለራሳቸው እንተወው፡፡ ጎበዝ ሯጭ በመንገዱ ግራና ቀኝ ያሉ ተመልካቾች ለሚሰነዝሩበት ነገር ሁሉ መልስ  እሰጣለሁ፤ ከእነርሱም ጋር ጊዜዬን አጠፋለሁ ካለ እንኳንስ ሊያሸንፍ ሩጫውን አይቀጥልም፡፡ በለውጥ መንገዳችን ላይ በሚገጥሙን አላፊ ነገሮች ጋር ጉልበት አንጨርስ፡፡ አይነተኛው ትኩረታችን አይነተኛው ግባችን ላይ ይሆን
ዘንድ የምንወስንበት ታሪካዊ ምእራፍ ላይ እንገኛለን፡፡
ዮሐንስ ለፈሪሳውያን፣ ለሰዱቃውያን ለግብር ሰብሳቢዎችና ለወታደሮች የነገራቸው ነገር የተጋነነም፣ የወረደም አይደለም፡፡ ማረም ያለባቸውን ነገር ብቻ ነገራቸው፡፡ ዛሬ በለውጥ ጉዟችን ወቅት አንዱ ልንታገለው የሚገባን ነገር ስሜታችንን ነው፡፡ ስሜት ዕውቀትን ከገዛው ኃይልና ጥላቻን ይወልዳል፡፡ ዕውቀት ስሜትን ከገዛው ግን ጥበብና ብልሐትን ያመጣል፡፡ ‹ለሰይጣንም እንኳን ቢሆን የሚገባውን ስጠው› ይባላል፡፡ አንዳንድ ነገሮች ምንም ያህል ቢያናድዱን፣ ምንም ያህል ቢያንገፈግፉን፣ ምንም ያህል እንድንጠላቸው የሚያደርጉ ስሜቶች ቢመጡብን የምንናገረውና የምንሰጠው አስተያየት ግን ልከኛ መሆን አለበት፤ እንደ ቅዱስ ዮሐንስ፡፡ የማይገባን ነገር መናገር
ተናጋሪውንም አይጠቅምም፤ ሰሚውንም አያንጽም፡፡
ዮሐንስን ዛሬ የምናስታውሰው በምንድን ነው? በአጥማቂነቱ ነው፡፡ ዋናው ተልዕኮው እርሱ ነበርና፡፡ ስለ እርሱ የተሳሉት ሥዕሎች ሁሉ የሚያሳዩት የእርሱን ዋና ተልዕኮ ነው፡፡ ከፈሪሳውያንና ከሰዱቃውያን፣ ከቀራጮችና
ከወታደሮች ጋር የነበረውን ነገር አያሳዩም፡፡ ሰው የሚለካው፣ የሚታሰበውም በዋናው ተልዕኮው ስኬት ነው፡፡
ይህ ትውልድ የሚታሰበው ዛሬ የተፈጠረውን ለውጥ ከሚፈለገው ግብ ላይ ካደረሰው ነው፡፡ በለውጡ መንገድ
ላይ እዚህም እዚያም ከሚነሡ ነገሮች ጋር የተነታረከውና የተጋጨው የትውልዱ መታሰቢያ አይሆንም፡፡ የሚለካውና የሚታሰበው በለውጡ ስኬት መጠን ነው፡፡ የዚህ ትውልድ ዋናው ተልዕኮም ለውጡን እና ለውጡን ተከትሎ የምናገኘውን በረከት በአግባቡ በመራበት፣ በተረዳበት እና ለፍሬ ባበቃበት ልክ እና መጠን ነው፡፡ በየዕለቱ
የሚፈጠሩ አታካራዎችን ትተን እንደ ዮሐንስ በዋናው ተልዕኳችን ላይ ጊዜያችንን እናጥፋ፡፡ ዮሐንስ ክርስቶስን
ለማጥመቅ የቻለው እየተከራከረ፣ እየተወዛገበ፣ ፈሪሳውያንና ሰዱቃውያን በቀደዱለት ቦይ መፍሰስን ምርጫው አድርጎ አይደለም፤ በፍጹም፡፡ እዚያው በዮርዳኖስ ወንዝ፣ በዋናው ተልዕኮው ላይ ተሠማርቶ እያጠመቀ ነበር፡፡
ያጠምቅበት የነበረው ሥፍራ ከባሕር ወለል በታች የሚገኝ እና ፍጹም በረሀ ቢሆንም እርሱ ግን ሁሉንም ተቋቁሞ ዋናው ተልእኮው ላይ ጸንቶ ነበር፡፡ ዮሀንስንም ዮሀንስ የደረገው እና በዘመናት መሀል በአማኞች ልብ ውስጥ የተከለውም ቁልፍ ሚስጥር ዋናው አላማው ላይ የመተከሉ እውነት ነው፡፡
ትኩረታችንን በለውጥ ሥራችን ላይ አድርገን፣ የሚመጡብንን የግራ ቀኝ ጉሸማዎች እያለፍን፣ በሙሉ ዐቅማችንየሚገባንን ከሠራን የምፈልገውን ማግኘታችን አይቀሬ ነው፡፡ ከቦታችን ሊያናውጡን፣ ከዋናው ተልዕኳችንም
ሊያዘናጉን ብዙ እንቅፋቶች ሊፈታተኑን ይችላሉ፡፡ አንዳንዶች በፈተና፣ ሌሎችም በሙገሣ ልባችንን ሊወስዱ
ይፈልጋሉ፡፡ እኛ ግን በብዙ መሰናክሎች ተከቦ፣ ሜዳልያውን እያሰበ፣ ወደ ሩጫው ፍጻሜ እንደሚገሠግሥ ሯጭ ከፊታችን ያለውን ውብ ቀን እና በጥረታችንም የምናስመዘግበውን ጣፋጭ ድል እያሰብን በጽናት ልንሮጥ
ይገባል፡፡ በጊዜያዊ እና አልፎ ሂያጅ ነገሮች ላይ ማተኮር ውጤታችንንም ታሪካችንንም ጊዜያዊ አድርጎት ይቀራል::
በልፋታችን፣ በትግላችን እና በብርታታችን የምንቋደሰው ድል የሁላችንም የመሆኑን ያህል ተግዳሮት እና  ፈተናውም የሁሉም ኢትዮጵያ ልጆች እንቅፋት መሆኑን በመረዳት እጅ ለእጅ ተያይዘን በፍቅር እና በመደመር ልንሻገረው ይገባል፡፡
ጥምቀት የሽግግር ወቅትም ነው፡፡ ለዓለም ሳይገለጥ የቆየው ክርስቶስ ለዓለም የተገለጠበት ድንቅ በዓል ነው፡፡
ለዚህም ነው የመገለጥ ወይም የአስተርእዮ በዓል የሚባለው፡፡ ጥምቀት መገለጥ ቢሆንም ክርስቶስ ለሁሉም
የተገለጠው ግን ከተጠመቀ ከዐርባ ሦስት ቀናት በኋላ ነው፡፡ ክርስቶስ በተወለደበትና ለዓለም በተገለጠበት ጊዜያት
መካከል ብዙ ዘመን አልፏል፡፡ አንድ ነገር የሚጀመርበትና የሚገለጥበት ጊዜ ይለያያል፡፡ በዚህች ሀገር ውስጥ
ለውጥ ለማምጣት ትግሉ ከተጀመረ ቆይቷል፡፡ ለውጡ ሕጋዊና ተቋማዊ ሆኖ የተገለጠው ግን በቅርቡ ነው፡፡
ክርስቶስ በዮርዳኖስ ወንዝ ተጠምቆ ለዓለም ከተገለጠ በኋላ ዐርባ የሽግግር ቀናት አልፈዋል፡፡ በነዚያ ዐርባ
የሽግግር ቀናት ብዙ ፈተናዎች ነበሩ፡፡ ብዙ ጥያቄዎችም ነበሩ፡፡ ያለንበት ጊዜም እንደዚያው ነው፡፡ የጀመርነው
የለውጥ ሂደት ሁሉም እስኪረዳው፣ ሁሉንም እስኪነካ፣ በሁሉም ቤት እስኪገባ ድረስ ብዙ ፈተናዎች፣ ብዙ
ጥያቄዎች ይኖራሉ፡፡ እርግጠኛ የምንሆነው ዋና ጉዳይ ግን ሁሉንም ፈተናዎቻችንን በድል የማለፋችን ነገር
ማለፋችን እርግጥ መሆኑን ነው፡፡
ጥምቀት ለእኛ ለኢትዮጵያውያን ልዩ በዓላችን ነው፡፡ ከከተራ ቀን ጀምረን ውኃ ባለበት ሜዳ ተሰብስበን
እናከብረዋለን፡፡ ኢትዮጵያችን የሁላችንም መሆኗን የምናሳይበት በዓላችን ነው፡፡ ‹ለጥምቀት ያልሆነ ቀሚስ…›
ብለን የየባህላችንን አልባሳት ለብሰን የምንወጣበት ደማቅ በዓላችን ነው፡፡ የሁላችንም ቋንቋ፣ የሁላችንም ዜማ
በአንድ መስክ ላይ ኅብር ሆኖ የሚቀርብበት የመደመር በዓል ነው፡፡ እዚህ አማርኛ፣ እዚያ ትግርኛ፣ እዚያ
ወላይትኛ ፣ እዚያ ጉራግኛ፣ እዚያ አገውኛ፣ እዚያ ሲዳምኛ፣ እዚያ ሶማልኛ፣ እዚያ ኦሮምኛ፣ እዚያ ኩናምኛ፣
እዚያ አፋርኛ፣ እዚያ በርትኛ፣ እዚያ አኝዋክኛ ይዜማል፡፡ ሁሉም ያለውን ይዞ ይወጣል፡፡ አንዱ ወደ ሌላው
ሄዶ ይጋራል፤ የራሱንም ያጋራል፡፡ መደመር ይሄ ነው፡፡ የጥምቀት በዓል ውበት ከመደመር ዕሴቱ የሚመነጭ
ነው፡፡ ‹የነብርን ጅራት አይዙም፤ ከያዙም አይለቁም› እንደሚባለው የለውጥ ጉዟችንን ይዘናል፤ የለውጡ ፋና
ይበልጥ እየተገለጠ በሄደ ቁጥር ችግሮቻችንም ይበልጥ እየቀነሱ ይሄዳሉ፡፡ በዋናው ተልዕኳችን ላይ አተኩረን
ጋሬጣዎችንና ዕንቅፋቶችን ካለፍናቸው ከባሕር ወለል በታች የጀመርነውን ለውጥ ከከፍታ በላይ እንጨርሰዋለን::
የምንጠብቀውም ሆነ የማንጠብቀው ችግር ከምንጓጓለት ግብ እንዳያስቀረን ትኩረታችንን በለውጥ ሂደታችን ላይ
እናድርግ፡፡ ያንን ካደረግን በጥምቀት መስክ ላይ የምናያትን ኢትዮጵያ በሁሉም መስኮች ላይ እናያታለን፡፡
ኢትዮጵያ በልጆቿ ጥረት ታፍራ፣ ተከብራና በልጽጋ ለዘላለም ትኑር!”
ፈጣሪ ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይባርክ!
መልካም በዓል!
አመሰግናለሁ፡፡
ጥር 10፣ 2011 ዓ.ም
https://ethiopianege.com/archives/8167

“የጥምቀት በዓል አከባበር በኢትዮጵያ……..”

 
“የጥምቀት በዓል አከባበር በኢትዮጵያ……..”


ጥምቀት በኢትዮጵያ (Ethiopian Epiphany Festivals )
በኢትዮጵያ አመታትን ጠብቀው የሚከበሩ ሀይማኖታዊ በዓላት ከእምነት ፋይዳቸው ባለፈ በውስጣቸው በያዙት መስህባዊ ተፈጥሮ ምክንያት በርካት የውጪ እና የሀገር ውስጥ ጎብኚዎችን ይስባሉ፡፡ ከእነዚህ ውስጥ አንዱ ደግሞ የጥምቀት በዓል ነው፡፡ የስነ መለኮት ምሁራን ጥምቀት ለሚለው ቃል መነከር ፣ መታጠብ ፣ መረጨት እና  የመሳሰሉትን ትርጓሜዎች ይሰጡታል፡፡የጥምቀት ዋዜማ ከተራ ይባላል፡፡ የከተራ እለት/ ጥር 10 ማለት ነው/ ከቀኑ 9 ሰዓት ጀምሮ በሚሰማው የደውል ጥሪ ታቦታቱ ፤ የተለያዩ ህብረ ቀለማት ያላቸው አልባሳት በለበሱ ህዝበ ክርስቲያን ታጅበው ጉዞአቸውን ወደ ጥምቀተ ባህር ያደርጋሉ፡፡

በሀገራችን ታቦት ተሸክሞ ፣ ወንዝ ወርዶ የክርስቶስን በዓለ ጥምቀት ማክበር የተጀመረው በአፄ ገብረመስቀል ዘመነ መንግስት እንደሆነ ሊቃውንት ያስረዳሉ፡፡ ይህንን ታሪክ በመከተል አፄ ነዖድም(1486 – 1500 ዓ.ም) ማንኛውም የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሃይማኖት ተከታይ የሆኑ ሁሉ ታቦተ ህጉን ወደ ጥምቀተ – ባህሩ በሚወርድበት ጊዜ እና ከጥምቀተ – ባህሩ ወደ ቤተ መቅደሱ በሚመለስበት ጊዜ አጅቦ መውረድ እና መመለስ እንዳለበት አዋጅ አስረግረው ነበር፡፡ በአዋጁ መሰረትም ህዝቡ በየአመቱ ታቦተ ህጉን በማጀብ ወንዶች በጭፈራ እና በሆታ፣ ሴቶች ደግሞ በእልልታ ሲያከብሩ ኖረዋል ፤ አሁንም እያከበሩት ይገኛል፡፡

በከተራው ዕለት ድንኳን ተተክሎ ፣ ዳሱ ተጥሎ እና ውኃው ተከትሮ ሁሉም ነገር ከተስተካከለ በኋላ፤ ታቦተ ህጉ የሚንቀሳቀስበት ሰዓት ሲደርስ የየቤተ መቅደሱ ታቦታት በወርቅ እና በብር መጎናፀፊያ እየተሸፈኑ ፤ በተለያየ ህብር በተሸለሙ የክህነተ አልባሳት በደመቁ ካህናት እና የመፆር መስቀል በያዙ ዲያቆናት ከብረው፣ ከቤተ መቅደስ ወደ አብሕርት/ መጥማቃት/ ለመሄድ ሲነሱ መላው አብያተ ክርስቲያናት የደውል ድምፅ ያሰማሉ፡፡ ምዕመናንም ከልጅ እስከ አዋቂ በአፀደ ቤተ ክርስቲያን እና ታቦታቱ በሚያልፉባቸው መንገዶች ለጥምቀት ያልሆነ ቀሚስ እንደሚባለው ያማረ ልብሳቸውን ለብሰው በዓሉን ያደምቃሉ፡፡


ታቦታት ከቤተ መቅደሳቸው ወጥተው በህዘበ – ክርስቲያኑ ታጅበው ማደሪያ ቦታቸው ይደርሳሉ፡፡ በዚያን ጊዜ ዳቆናት እና ቀሳውስት በባህረ ጥምቀቱ ዙሪያ ሆነው ከብር የተሰሩ መቋሚያ እና ፅናፅን እንዲሁም ከበሮ ይዘው በነጫጭ እና በወርቅ ቀለም ባሸበረቁ እጥፍ ድርብ አልባሳት አምረው እና ተውበው፤የክርስቶስን የጥምቀት ታሪክ የሚያወሱ ወረብ እና መዝሙሮችን ጣዕም ባለው ዜማ ያቀርባሉ፡፡ ሌሊቱን ስብሀተ – እግዚአብሔር ሲደርስ አድሮ ከዚያም ስርዓተ ቅዳሴው ይፈፀማል፡፡ በወንዙ /በግድቡ/ ዳር ፀሎተ- አኩቴት ተደርሶ 4ቱ ወንጌላት ከተነበቡ በኋላ ባህረ ጥምቀቱ በብፁዓን አባቶች ተባርኮ ለተሰበሰበው ህዝበ – ክርስቲያን ይረጫል፡፡ ለዚህ በዓል ህዝበ ክርስቲያኑ ልዩ ትኩረት ይሰጠዋል፡፡ ምክንያቱም በዓሉ እየሱስ ክርስቶስ በፈለገ ዮርዳኖስ የተጠመቀበትን ተምሳሌት በማሰብ ስለሚከበር፡፡

የጥምቀት በዓል ሀይማኖታዊ ስርዓቱን ከባህላዊ ወግ እና ስርዓት ጋር አጣምሮ የያዠ ነው፡፡ በዚህም በርካታ ብሄር ብሄረሰቦች ህብረ – ቀለማዊ የሆነ ጨዋታቸውን በልዩ ልዩ ቋንቋዎች ያቀርባሉ፡፡ በዓሉን ለማክበር ወደ ጥምቀተ ባህር የሚሄዱ ሰዎች ከበዓሉ በፊት ተዋወቁም አልተዋወቁም በዚያን ዕለት በጋራ ሆነው ጥዑም ዜማዎችን ያንቆረቁራሉ፡፡ ይህ ዕለት ማንም ሰው ሳያፍር እና ሳይሸማቀቅ የውስጡን የሚገልፅበት እና በጋራ የሚጫወትበት ዕለት ነው፡፡ ከዚሁ ጋር ተያይዞም በጓደኝነት ለመተጫጨት ለሚፈልጉ ወጣቶች መልካም አጋጣሚን ይፈጥራል፡፡ ህዝበ – ክርስቲያኑ ይህንን በዓል ዘር እና ቀለም ሳይለዩ በአንድነት ያከብሩታል፡፡ በመሆኑም በዓሉ ህዝብን ያቀራርባል፤ የመረዳዳት ባህልንም ያሳድጋል፡፡


የጥምቀት በዓልን ለማክበር የተለያዩ ሀገር ዜጎች ፣ ዲፕሎማቶች፣ አምባሳደሮች እና ከፍተኛ ባለስልጣናት እንዲሁም የቤተክርስቲያን አባቶች እና ምዕመናን ይታደማሉ፡፡ ይህ በዓል በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች የሚከበር ቢሆንም በተለይ በአፄ ፋሲል መዋኛ ፣ በላልይበላ ፣ በመቀሌ ፣ በአክሱም እና በአዲስ አበባ ከተሞች በተዘጋጀላቸው የክብር ቦታ ህዝበ – ክርስቲያኑ ከውጪ ከሚመጡ ቱሪስቶች ጋር በዓሉን በደመቀ ሁኔታ ያከብሩታል፡፡ ታዲያ በዚህ በዓል ላይ ያስገረማቸውን ነገር በማስታወሻነት ለማስቀመጥ የተለያዩ ሰዎች የፎቶ እና የቪዲዮ ካሜራዎቻቸውን ደግነው እያነሱ እና እየቀረፁ ያስቀራሉ፡፡  በመጨረሻም በሀገራችን የሚከበሩ ሀይማኖታዊ በዓላት የመረዳዳት እና የመደጋገፍ ባህልን ያዳብራሉ፡፡ ከዚህም ባሻገር አገሪቱ ከቱሪዝም ኢንዱስትሪው ተጠቃሚ እንድትሆን ያስችሏታል፡፡ ስለዚህ ተገቢውን ትኩረት ልንሰጣቸው ይገባል፡፡

http://ethiopiaanything.com/2018/01/17/%e1%88%88%e1%8c%a5%e1%88%9d%e1%89%80%e1%89%b5-%e1%89%a0%e1%8b%93%e1%88%8d-%e1%8a%a0%e1%8a%a8%e1%89%a3%e1%89%a0%e1%88%ad-%e1%89%a0%e1%8a%a2%e1%89%b5%e1%8b%ae%e1%8c%b5%e1%8b%ab/

Saturday, December 28, 2019

እንኳን ለቅዱስ ገብርኤል በዓል በሰላም አደረሳችሁ

በስመአብ ወወልድ ወመንፈስቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን
እንኳን ለቅዱስ ገብርኤል በዓል በሰላም አደረሳችሁ

የቅዱስ ቂርቆስ እና ቅድስት ኢየሉጣ ተጋድሎ

በመጽሐፈ ስንክሳር፣ በድርሳነ ገብርኤል እና በገድለ ቂርቆስ ወኢየሉጣ እንደ ተመዘገበው ሐምሌ ፲፱ ቀን ቅዱስ ቂርቆስ እና ቅድስት ኢየሉጣ በሰማዕትነት መከራ የተቀበሉበት፤ ስማቸውን የሚጠሩ፣ ዝክራቸውንም የሚዘክሩ ምእመናን ይቅርታን፣ ምሕረትን እንደሚያገኙ ጌታችን አምላካችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለእነዚህ ቅዱሳን ቃል ኪዳን የሰጠበት ቀን ነው፡፡ መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ከእግዚአብሔር ዘንድ ተልኮ የተራዳቸውም በዚሁ ዕለት ነው፡፡ በዛሬው ዝግጅታችን የሰማዕታቱ ቅዱስ ቂርቆስንና ቅድስት ኢየሉጣን ገድል በአጭሩ እናስታውሳችኋለን፤
ቅድስት ኢየሉጣ በሮም ግዛት በሚገኝ አንጌቤን በሚባል አገር በፈሪሃ እግዚአብሔር፣ በክርስትና ሃይማኖት እና በበጎ ምግባር ጸንታ ትኖር የነበረች ደግ ሴት ናት፡፡ በሥርዓት ያሳደገችው ቂርቆስ የሚባል ሕፃን ልጅም ነበራት፡፡ ይህቺ ቅድስት የዘመኑን አረማዊ መኰንን እለእስክንድሮስን በመፍራቷ ከልጇ ጋር ከሮም ወደ ጠርሴስ በተሰደደች ጊዜ መኰንኑ እነርሱ ከሚገኙበት አገር ገብቶ ክርስቲያኖችን እያሳደደ መግደል ጀመረ፡፡ የንጉሡ ወታደሮችም እግዚአብሔርን እንዲክዱ፤ ለጣዖት እንዲሰግዱ ቅድስት ኢየሉጣንና ቅዱስ ቂርቆስን አስፈራሯቸው፡፡ ቅዱሳኑ ግን ሃይማኖታቸውን ለመለወጥ ፈቃደኛ አልኾኑም ነበር፡፡ በዚህም መኰንኑ ተቈጥቶ በዓይንና በአፍንጫቸው ውስጥ ጨውና ሰናፍጭ በመጨመር፤ በጋሉ የብረት ችንካሮች በመቸንከርና መላ ሰውነታቸውን በመብሳት በብዙ ዓይነት መሣሪያ አሠቃያቸው፡፡ እግዚአብሔርም የጋሉ ብረቶችን እንደ ውኀ ያቀዘቅዝላቸው፤ ሥቃያቸውንም ያቀልላቸው ነበር፡፡
በሌላ ጊዜም በገመድ አሳሥሮ ንጉሡ ሲያስጨንቃቸው ከቆየ በኋላ ራሳቸውን ከቆዳቸው ጋር አስላጭቶ እሳት አነደደባቸው፡፡ ዳግመኛም ከትከሻቸው እስከ እግራቸው ድረስ በሚደርሱ ችንካሮች ቸነከራቸው፡፡ በዚህ ጊዜ የእግዚአብሔር መልአክ ቅዱስ ገብርኤል ከእግዚአብሔር ዘንድ ተልኮ ከሥቃያቸው አድኗቸዋል፡፡ አሁንም ቀኑን ሙሉ በልዩ ልዩ የሥቃይ መሣሪያዎች ቢያስጨንቃቸውም የእግዚአብሔር ኃይልና የቅዱስ ገብርኤል ተራዳኢነት አልተለያቸውም ነበርና ምንም ዓይነት ጉዳት አልደረሰባቸውም፡፡ እንደ ገናም በመጋዝ ሰንጥቀው በብረት ምጣድ በቆሏቸው ጊዜ ጌታችን ከሞት አነሣቸውና በመኰንኑ ፊት ድንቅ ተአምራትን አደረጉ፡፡ ከተአምራቱ መካከልም ሕፃኑ ቅዱስ ቂርቆስ የመኰንኑን ጫማ በጸሎት ወደ በሬነት እንዲቀየር ማድረጉ ተጠቃሽ ሲኾን፣ መኰንኑ በተአምራቱ ተቈጥቶ የቅዱስ ቂርቆስን ምላስ አስቈርጦታል፤ ጌታችንም ምላሱን አድኖለታል፡፡
ዳግመኛም በፈላ የጋን ውኀ ውስጥ ቅዱሳን ቂርቆስና ኢየሉጣን ሊጨምሯቸው ሲሉ ቅድስት ኢየሉጣ በፈራች ጊዜ ቅዱስ ቂርቆስ ‹‹እናቴ ሆይ አትፍሪ፤ አናንያ፣ ዓዛርያና ሚሳኤልን ከእሳት ነበልባል ያዳናቸው እግዚአብሔር እኛንም ከዚህ የፈላ ውኀ ያድነናል›› እያለ ያረጋጋትና በተጋድሎዋ እንድትጸና ወደ እግዚአብሔር ይጸልይላት ነበር፡፡ ከዚህ በኋላ ተያይዘው ወደ ጋኑ ውስጥ ገቡ፡፡ ያ ውኀም እንደ ውርጭ ቀዘቀዘ፡፡ ደግሞም ወታደሮቹ መንኰራኵር ባለበት የብረት ምጣድ ውስጥ አስገብተው ሥጋቸው እስኪቈራረጥ ድረስ በጎተቷቸው ጊዜ ቅዱስ ገብርኤል አድኗቸዋል፡፡ በመጨረሻም ከእግዚአብሔር ቃል ኪዳን ተቀብለው በመንፈቀ ሌሊት አንገታቸውን ተቈርጠው በሰማዕትነት ዐርፈዋል፡፡ እስከ ሞት ድረስ በታመኑበት ተጋድሏቸውም ከእግዚአብሔር ዘንድ የሕይወትን አክሊል ተቀብለዋል፡፡
በአጠቃላይ ቅዱስ ቂርቆስና ቅድስት ኢየሉጣ የዚህን ዓለም ጣዕም በመናቅ ‹‹ሞት ቢኾን፣ ሕይወትም ቢኾን፣ መላእክትም ቢኾኑ፣ ግዛትም ቢኾን፣ ያለውም ቢኾን፣ የሚመጣውም ቢኾን፣ ኃይላትም ቢኾኑ፣ ከፍታም ቢኾን፣ ዝቅታም ቢኾን፣ ልዩ ፍጥረትም ቢኾን በክርስቶስ ኢየሱስ በጌታችን ካለ ከእግዚአብሔር ፍቅር ሊለየን እንዳይችል ተረድቼአለሁ፤›› (ሮሜ. ፰፥፴፰-፴፱) በማለት ቅዱስ ጳውሎስ የተናገረውን ቃል በተግባር በማሳየት ለክርስቶስ ፍቅር ሲሉ ራሳቸውን ለመከራና ለሞት አሳልፈው ሰጥተዋል፡፡ ቅዱሳኑ ተጋድሏቸውን እስኪፈጽሙ ድረስም ቅዱስ ገብርኤል አልተለያቸውም፡፡ በቅዱስ ገብርኤል ተራዳኢነት ቅድስት ኢየሉጣና ቅዱስ ቂርቆስ ብቻ ሳይኾኑ ብዙ ምእመናንም ተጠቅመዋል፡፡ ስሙ በሚጠራባቸው ገዳማትና አድባራት መልአኩ የሚያደርጋቸው ድንቅ ድንቅ ተአምራት ለዚህ ማስረጃዎች ናቸው፡፡ ይህም ቅዱሳን መላእክት በእግዚአብሔር ስም መከራ የሚቀበሉ ምእመናንን እንደሚጠብቁና ከልዩ ልዩ ደዌ እንደሚፈውሱ የሚያስረዳ ታሪክ ነው፡፡
እኛም በሃይማኖታችን ምክንያት መከራ ባጋጠመን ጊዜ ቈራጥ ልብ ያለው ሕፃኑ ቅዱስ ቂርቆስ ‹‹እናቴ ሆይ አትፍሪ›› እያለ እናቱን በመከራ እንድትጸና እንዳረጋጋትና ለሰማዕትነት እንድትበቃ እንዳደረጋት ዅሉ፣ ዘለዓለማዊውን የእግዚአብሔርን መንግሥት በአንድነት ለመውረስ እንድንችል ‹‹አይዞህአይዞሽአትፍራአትፍሪ›› በመባባል በዚህ ዓለም የሚገጥመንን መከራ ታግሠን፣ እስከ ሞት ድረስ በሃይማኖታችን ጸንተን መኖር ይገባናል፡፡ ክርስትና ለብቻ የሚጸደቅበት መንገድ ሳይኾን በጋራ ዋጋ የሚያገኙበት የድኅነት በር ነውና፡፡ ከዚሁ ዅሉ ጋርም ቅዱስ ቂርቆስንና ቅድስት ኢየሉጣን የተራዳው የእግዚአብሔር መልአክ ቅዱስ ገብርኤል በአማላጅነቱ እንዲጠብቀን ‹‹በተአምኖ ንሴፎ ትንባሌ ዚአከ መዓልተ ወሌሊተ፤ በእግዚአብሔር ታምነን በቀንም በሌሊትም የአንተን ልመና ተስፋ እናደርጋለን›› እያልን ዘወትር ልንማጸነው ያስፈልጋል፡፡ እርሱ ከፈጣሪው ከእግዚአብሔር በተሰጠው ቃል ኪዳን መሠረት ከሚደርስብን ልዩ ልዩ መከራና ሥቃይ ያድነናልና፡፡ ‹‹የእግዚአብሔር መልአክ በሚፈሩት ሰዎች ዙርያ ይሠፍራል፤ ያድናቸውማል፤›› ተብሎ እንደ ተጻፈ (መዝ. ፴፬፥፯)፡፡ ይህን እንድናደርግም የቅዱሳን ተራዳኢነት አይለየን፡፡ የቅዱስ ገብርኤል፣ ቅድስት ኢየሉጣ እና ቅዱስ ቂርቆስ ጸሎታቸው፣ ምልጃቸው ይጠብቀን፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር


Thursday, December 19, 2019

እሪዮ / ምሽግ

እሪዮ / ምሽግ

በአንድራቻ ወረዳ፤ ጨገቻ ቀበሌ፤ ከወረዳው ዋና ከተማ ጌጫ በ7ኪሜ ርቀት ላይ ይገኛል፤
የሸካ ንጉስ ግባጋዮች ዘመን ጠላት ሲመጣ  /ጎነኮሶ/ ጠላት መምጣቱን ለማሰማት ጥሪ ያስተላልፋሉ፤
ጠላት ቀጥታ ሲመጣ በተቆፈረው ምሽግ /እርዮ/ ውስጥ እንዲገባ መንገዱን ጠርገው ያስተካክላሉ፤ ከዚያም በኋላ ፈረሰኞች ጋሻና ጦር ይዘው እየጋለቡ ሄደው በተቆፈረው ጉድጓድ ዉስጥ ሰምጠው ይቀራሉ፤ ጉድጓዱ በግምት ጥልቀቱ ከ5-6 ሜትር የሚሆን ሲሆን የተለያዩ ስለት ያላቸው ቁሳቁሶችን ከቸከሉ በኋላ ጠላት ገብቶ የሚማረክበት ሂደት እንደነበረ የታሪክ አዋቂዎች ይናገራሉ፡፡

ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ከ100 ተፅዕኖ ፈጣሪ ሴቶች አንዷ ሆኑ

ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ከ100 ተፅዕኖ ፈጣሪ ሴቶች አንዷ ሆኑ

ፎርብስ መጽሔት ፕሬዚዳንት ሳህለ ወርቅ ዘውዴን ከ100 የዓመቱ ተፅዕኖ ፈጣሪ ሴቶች መካከል መርጧቸዋል፡፡ ፕሬዚዳንቷ ከመቶ የዓመቱ ተፅዕኖ ፈጣሪ ሴቶች መካከል የተመረጡ ብቸኛ አፍሪካዊት ናቸው፡፡ ፎርብስ ካወዳደራቸው ሴቶች መካከልም ፕሬዚዳንት ሳህለ ወርቅ 93ኛ ደረጃን ይዘዋል፡፡
ዓምና ጥቅምት ወር ላይ የመጀመርያ ሴት ፕሬዚዳንት ሆነው የተመረጡት ፕሬዚዳንት ሳህለ ወርቅ፣ አገራቸውን በዲፕሎማሲው ዘርፍ ለረዥም መታት ያገለገሉ ናቸው፡፡ በተለያዩ ዓለም አቀፍ ድርጅቶችም በልዩ ልዩ ኃላፊነት ደረጃዎች ሠርተዋል፡፡
አምና ከተመረጡ ተፅዕኖ ፈጣሪ ሴቶች መካከል አፍሪካዊቷ ኢሳቤላ ዶ ሳንቶስ አንዷ ነበሩ፡፡ ኢሳቤላ የቀድሞ የአንጎላ ፕሬዚዳንት ሆዜ ኤድዋርዶ ዶ ሳንቶስ ልጅ እንደሆኑ ፎርብስ አስታውሷል፡፡
የጀርመኗ አንጌላ መርኬል፣ ከፈረንሣይ ክርስቲን ላጋርዴ፣ ከአሜሪካ ናንሲ ፔሎሲ በዓመቱ ተፅዕኖ ፈጣሪ ሴቶች ዝርዝር ውስጥ ቀዳሚ በመሆን ከአንድ እስከ ሦስተኛ ደረጃ ይዘዋል፡፡ ሜሊንዳ ጌትስ ስድስተኛ፣ ኦፕራ ዊንፍሬይ 20ኛ ሆነው ሲመረጡ፣ የአየር ንብረት ጥበቃ ተሟጋቿ የ16 ዓመቷ ታዳጊ ግሬታ ተንበርግ ደግሞ 100ኛ ሆናለች፡፡